ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኤሌክትሪክ ወደ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ወርዷል

የ2011 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ (አንደኛ ዲቪዝዮን) የመጨረሻ ሳምንት አንድ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአርባምንጭ 3-2 ተሸንፎ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መውረዱን አረጋግጧል።

ጨዋታው ተመጣጣኝ የሆነ እና በሁለቱም በኩል ኳሱን ይዘው ለመጫወት የሞከሩበት ነበር። በአርባምንጭ በኩል ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በዝተው ኳሱን በመያዝ ኤሌክትሪኮች ወደ ሜዳ ክፍላቸው እንዲገቡ በማድረግ ለፈጣን አጥቂዎቻቸው በሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር የፈጠሩት ታክቲክ ተሳክቶላቸው በ10ኛው ደቂቃ ጎል አዚዛ ታዬ ከግራ መስመር አፈትልካ በመነሳት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥራለች።

በጫና ውስጥ ሆነው ላለመውረድ ብርቱ ትግል ያደረጉት ኢትዮ ኤሌትሪኮች አርባምንጭ የመጀመርያ ጎላቸውን ባስቆጠሩበት መንገድ ዓለምነሽ ገረመው ከተከላካይ ጀርባ ያሻገረችውን ኳስ ዓይናለም ፀጋዬ ወደ ፊት ገፍታ በመሄድ በአስገራሚ ሁኔታ በግብ ጠባቂዋ አናት ላይ ኳሱን በመጣል ኢትዮ ኤሌክትሪክን አቻ አደረገች። ብዙም ሳይቆይ ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ ወርቅነሽ መልመላ አግኝታ ሳትጠቀም ቀርታለች።

ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች በ35ኛው ደቂቃ የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ አበባየሁ ጣሰው ከግብ ክልሏ ውጭ ኳስ በእጅ በመያዟ ተከትሎ በቀጥታ ቀይ ካርድ መውጣቷን ተከትሎ የቁጥር ብልጫውን ይጠቀማሉ ቢባልም የሆነው ግን ተቃራኒው ነበር። አርባምንጮች የቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም የመጫወት ፍላጎታቸው ጨምሮ በ43ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ትዕግስት አዳነ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራ 2-1 እየመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተጫዋች ቅያሪ ቢያደርጉም ቡድኑ የመውረድ ስጋት ውስጥ መሆኑ እና በአንድ ጎል መመራታቸው የፈጠረባቸው ተፅእኖ የሚፈለገውን እንቅስቃሴ ለማሳየት እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል። በተለይ ግብጠባቂዋ ገነት አንተነህ ተቀይራ እስከወጣችበት ጊዜ ድረስ ትሰራው የነበረው ስህተት ለዚህ ማሳያ ነው። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን የጎል አጋጣሚ ዓይናለም አግኝታ የግቡ አግዳሚ ቢመልስባትም ብዙም ሳይቆይ ተቀይራ የገባችው ዘይነባ ሰዒድ በ61ኛው ደቂቃ ከርቀት መትታ ባስቆጠረችው ጎል ሁለት አቻ መሆን ችለዋል።

የጨዋታው ፉክክር አይሎ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ያልገደባቸው አርባምንጮች 73ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ፀጋነሽ ወላና ግበጠባቂዋ እስራኤል ከተማን በማለፍ ባስቆጠረችው ማራኪ ጎል በድጋሚ መሪ ሆነዋል። በቀሩት ደቂቃዎች ጎል ፍለጋ ኤሌክትሪኮች ጥረት የአርባምንጭ የመከላከል ጥንካሬ አሳይቶን ጨዋታው በአርባምንጭ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽንፈቱን ተከትሎ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ወደ ሁለተኛ ዲቪዝዮን መውረዱን ያረጋገጠ ቡድን ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡