ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ባህር ዳር ከተማን በማሸነፍ በመሪነቱ ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማን ከባህር ዳር ያገናኘው ጨዋታ 4–0 ተጠናቋል።

ከጨዋታው አስቀድሞ የፋሲል ከነማ ደጋፊ ማኅበር ለባህርዳር ከተማ ደጋፊ ማህበር እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ስጦታ በማበርከት በደመናማ የአየር ፀባይ በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በባለሜዳው ፋሲል ከነማ የበላይነት የተጠናቀቀ ሲሆን ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት በመጠኑም ፈጠን ያለ ጨዋታ የተመለከትንበት፣ በፋሲል ከነማ  በኩል ተደጋጋሚ ወደ ግብ  የመድረስ ዕድሎችን ከዛም አልፎ ጎሎችን ያስመለከተም ነበር። ፋሲሎች በራሳቸው ሜዳ ኳስ በመመስረት የተሻለ ብልጫ ወስደው በመጫወት የተሻለ ሲሆኑ ገና በ3ኛው ደቂቃ ነበር በቀኝ መስመር በኩል ከኢዙ አዙካ ወደ ግብ የተሻማውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ በጭንቅላቱ ግሩም ጎል በማስቆጠር ነበር ጅማሪያቸውን ያሳመሩት።

ከጎሉ መቆጠር በኃላም ፋሲል ከነማዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲያደርጉ 10ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢሞክርም በጎሉ አናት ላይ ኳሶ ልትወጣ ችላለች። በ17ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል ኢዙ አዙካ ያሻማውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ቢሞክርም ወደ ሁለተኛ ግብ መቀየር አልተቻለም። ፋሲሎች አሁንም ጥቃታቸውን በመቀጠል 21ኛው ደቂቃ መሃል ላይ ሱራፌል ለኢዙ ያቀበለውን ኳስ ኢዙ አዙካ ወደ ሳጥን ተከላካዮችን አታሎ ይዞ በመግባት አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው አድኖበታል።

ከነዚህ ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ የጨዋታውን ሁለተኛ ግብ በ24ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ከአምሳሉ ጥላሁን የተሻማውን ኳስ በድንቅ ብቃት በጭንቅላቱ ግሩም ጎል ሙጂብ ቃሲም አስቆጥሯል። ከጎሉ በኋላም የባህርዳርን የጎል ክፍል በሙከራ ማጨናነቃቸውን ያላቆሙት ባለሜዳዎቹ ዐፄዎቹ 28ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ኤፍሬም ዓለሙ ወደ ጎል አክርሮ የማታውን ኳስ በባህር ዳር ተከላካዮች የተመለሰ ቢሆንም በድጋሚ በዛብህ መለዮ ኳሶን አግኝቶ ወደ ጎል ጠንካራ ምት ቢሞክርም ግብ ጠባቂው አድኖታል።

በጨዋታው ሙሉ ብልጫ ወስደው መጫወትን የቀጠሉት ዐፄዎቹ ሦስተኛውን ጎል በ31ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከሳጥን ውጭ ኢዙ አዙካ ራሱ ይዞት የገባውን ኳስ በሚገርም የአጨራረስ ብቃት አስቆጥሯል። ከዚህም ቀጥሎ ፋሲሎች በ33ኛው ደቂቃ አስደናቂ ቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው የሞከራት እንዲሁም 42ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን በግራ መስመር ኳሱን እየገፋ በመውሰድ በቀጥታ የሞከረው አስደጋጭ ሙከራ የሚጠቀሱ ሲሆኑ ወደ ግብ ሳይቀየሩ 3–0 እየመሩ ወደ እረፍት ሲያመሩ ባህርዳሮች አንድም ኢላማውን የጠበቀ ኳስ ሳይሞክሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ባለ አጨዋወት የጀመረ ሲሆን በሙከራ ደረጃ ፋሲሎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው በግሩም ሁኔታ ለሙጂብ ቃሲም ያሻገረለትን ኳስ ሙጂብ ወደ ግብ ቢሞክርም በግቡ አግዳሚ ወደ ውጪ ወጥቷል። በመልሶ ማጥቃት ባህርዳር ከነማዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ወርቁ በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ለቴዎድሮስ ሙላት ሲያቀብለው ቴዎድሮስ ሙላት ወደ ግብ አክርሮ የመታ ቢሆንም በፋሲል በረኛ ምርጥ ብቃት ጎል ከመሆን ታድጎታል። ፋሲሎችም በመልሶ ማጥቃት 50ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ከመሃል ወደ ግራ በኩል ለኢዙ አዙካ ቢያቀብልም ኢዙ አዙካ አክርሮ ወደ ጎል የሞከረውን ኳስ የግቡ አግዳሚ ገጭቶታል።

በ72ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ዮሴፍ ዳሙዬ ሳጥን ውስጥ በሚገርም ሁኔታ ለሙጂብ ቃሲም ያቀበለውን ኳስ ሙጂብ በጥሩ አጨራረስ ለራሱ ሁለተኛ ጎል ለክለቡ አራተኛውን ጎል በማስቆጠር ዐፄዎቹን ጮቤ አስረግጧል።

ባህር ዳር ከተማዎች በ77ኛው ደቂቃ ዳንኤል ኃይሉ ለጃኮራፋት ያሻማውን ኳስ ጃኮአራፋት ኳሶን ተቆጣትሮ ለደረጀ ሲያቀብለው ደረጀ አስደጋጭ ሙከራ ቢያረግም በቋሚው በኩል ወደ ውጭ ወጥቷል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ የተገኘውን ቅጣት ምት ደግሞ ዳንኤል ኃይሉ አክርሮ ሞክሮ ሳማኬ ሚኬል በድንቅ ብቃት አድኖታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በፋሲል ከነማ 4–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ ማሸነፉን ተከትሎ በ52 ነጥብ መሪነቱን ሲያጠናክር ባህር ዳር ከተማዎች በ37 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡