አአ ሀ-17 | ኤሌክትሪክ ከመሪው ያለውን ልዩነት ሲያጠብ አፍሮ ፅዮን፣ አዳማ እና ሀሌታ አሸንፈዋል

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድርር 18ኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው አፍሮ ፅዮን፣ አዳማ ከተማ፣ ሀሌታ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል።

03:00 በጎፋ ሜዳ የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያካሄዱት መከላከያ እና የአፍሮ ፅዮን ከአስደናቂ እንቅስቃሴ ጋር በአፍሮ ፅዮን 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ገና ጨዋታው ጅማሬ ነበር ኤርሚያስ አበበ ባስቆጠረው ጎል አፍሮ ፅዮኖች ቀዳሚ መሆን የቻሉት። በፍጥነት ጎል ቢቆጠርባቸው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ብዙ ያልቆዩት መከላከያዎች የአፍሮ ፅዮን ግብጠባቂ ኳስ ለማራቅ ከግብ ክልሉ ሲወጣ የሰራውን ስህተት ተከትሎ አቤል ሲሳይ መከላከያን አቻ ማድረግ ቻለ። ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር አስመልክቶን የቀጠለው ጨዋታ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ከአራት ደቂቃ በኋላ ምስግናው መላኩ በክፍት ሜዳ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ መከላከያን መሪ ማድረግ ችሏል። በየጨዋታዎቹ በግሉ መልካም እንቅስቃሴ በማድረግ ከአፍሮ ፅዮን ተጫዋቾች መካከል ጎልቶ መውጣት የቻለው አሸናፊ አክመል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የአፍሮ ፅዮንን ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር አቻ ሁለት አቻ ማድረግ ችሏል።

በጎሎች ታጅቦ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መከላከያን መሪ መሆን የቻሉበትን ጎል ምስጋናው መላኩ ለራሱ ሁለተኛ ለመከላከያ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ ምላሽ የሠጡት አፍሮ ፅዮኖች አሸናፊ አክመል ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ኳሱን ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ተረጋግቶ የበረኛውን አቋቋም በማየት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል ግሩም ጎል አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል። ድራማዊ ክንውን እያስመለከተን የቀጠለው ይህ ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ አሸናፊ አክመል ለራሱ ሐት-ትሪክ የሰራበትና አፍሮ ፅዮንን አሸናፊ ማድረግ ያስቻለበትን አራተኛ ወሳኝ ጎሉን በሚገርም አጨራረስ ብቃት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአፍሮ ፅዮን 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአፍሮ ፅዮን በኩል ቡድኑን በአምበልነት በመምራት እና በመከላከሉም እረገድ ትልቅ ሚና እየተወጣ የውድድር ዓመቱን የጨረሰው ተከላካዩ ይታገሱ ታሪኩ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ነው።

05:00 በቀጠለው የውድድር ዓመቱን የመጨረሻ ሌላ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ ከተማ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው አስቀድሞ አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአዳማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ተሳታፊ እንዲሆኑ በጠየቁት ጊዜ በውድድሩ እንዲሳተፉ በመፍቀዱ እና ለተደረገላቸው ሙሉ ድጋፍ የአዳማ እግርኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበስ መገርሳ ለአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተወካይ ለኢ/ር የኔነህ በቀለ የተዘጋጀውን ስጦታ አበርክተዋል።

ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ አንስቶ መሻሻል እያሳዩ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጎል በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ ነበሩ፤ ሚኪያስ ቡልቡላ ባስቆጠረው ጎል አማካኝነት። አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ብዙም ያልቆዩት አዳማዎች በልማደኛው ጎል አዳኛቸው ፍራኦል ጫላ አማካኝነት አንድ አቻ መሆን ችለዋል። ፍራኦል በውድድሩ ዓመት ያስቆጠራቸውን ጎሎች 28 በማድረስ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን የማጠናቀቅ እድሉን ከማስፋቱ ባሻገር ወደፊት ጠንክሮ ከሰራ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ተስፋኛ ተጫዋች መሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ ችሏል። ጨዋታው በጥሩ ምልልስ ቀጥሎ ዳዊት ግርማ የአዳማው ግብ ጠባቂ ኢዘዲን ዓሊ ስህተት ታክሎበት ለኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ወደ ጎል የሚደረጉ ምልልሶች በተደጋጋሚ በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ አዳማዎች በፈጥን እንቅስቃሴ ከቀኝ መስመር ወደ ጎል በመግባት ሙባሪክ ሸምሱ አዳማን ሁለት አቻ ማድረግ የቻለበትን ጎል አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ የአዳማ ከተማ ብልጫ የታየበት እና ሁለት አስገራሚ ጎሎች የተመለከትንበት ሆኖ አልፏል። ከቀኝ መስመር ተከላካዩ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ከሳጥን ውጭ የተቀበለውን ኳስ ቆርጦ በመምታት ነቢል ኑሪ እጅግ የሚገርም አዳማን መሪ ያደረገበትን ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። በአዳማ በኩል እንደ ፍራኦል ጫሉ ሁሉ ወደፊት ተስፋ ከሚደረግባቸው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል ነቢል ኑሪ አንዱ ነው።

በተለመደው የማጥቃት መንገዳቸው ከመስመር በመነሳት የግብ ዕድል የሚፈጥሩት አዳማዎች ሦስተኛ ጎላቸውን ባስቆጠሩበት መንገድ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ጌታያውቃል ከበደ ግሩም አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሌሎቹ የዛሬ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሠላምን 3-2 በማሸነፍ ከመድን ጋስ ያለውን ልዩነት ሲያጠብ ሀሌታ ኢ/ወ/ስ አካዳሚን 2-0 አሸንፏል።

የውድድሩ መደበኛ ጨዋታዎች የተጠናቀቁ ሲሆን ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ከተካዱ በኋላ ቻምፒየኑ ቡድን የሚለይ ይሆናል።

ቅዳሜ ሰኔ 8
ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ቅዳሜ ሰኔ 15
ሀሌታ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ኢትዮጵያ መድን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡