ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በእጅጉ ተጠግቷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 20ኛ ሳምንት ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አንድ አግሩን ያስገባበትን፤ ለገጣፎ ለገዳዲም ልዩነቱን ያስጠበቀበትን ድል አስመዝግበዋል።

ሰበታ ከተማ 1-0 ደሴ ከተማ

(በዳዊት ፀሐዬ)

የሰበታ ከተማ ደጋፊዎች ለደሴ ከተማ ተጫዋቾችና አሰልጣኝ ቡድን አባላት ባበረከቱት የአበባ ስጦታ የጀመረውና ጫላ ድሪባ ለሰበታ ባደረገው አስደንጋጭ ሙከራ የጀመረው ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን ያስመለከተ ነበር። የባለሜዳዎቹ አንጻራዊ የበላይነት በተስተዋለበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች በናትናኤል ጋንቹላ አቤል ታሪኩና ኢብራሂም ከድር አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ በአንጻሩ በመልሶ ማጥቃት የተሻሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉት ደሴዎች በ15ኛው ደቂቃ አሸናፊ ከበደ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ የሰበታው ግብጠባቂ ያዳነበት እንዲሁም በ33ኛው ደቂቃ አላዛር ዝናቡ በግንባሩ የሞከረውና በተመሳሳይ ግብጠባቂው የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ሰበታ ከተማዎች በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ወደ ግራ መስመር ባደላ መልኩ ፈጣን የመስመር ላይ አጨዋወት የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ መስመር ሲያስቸግሩ ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ በመጀመሪያው ደቂቃዎች ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብን ፈልገው የገቡት ሰበታዎች ከፍተኛ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ላይም ከደሴ ከተማ ተጫዋቾች ተነጥቆ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ኢብራሂም ከድር ወደ ግብ ሲልካት የደሴው ግብጠባቂ ሙሴ ገ/ኪዳን ተፍቶት በቅርብ ርቀት የነበረው ጫላ ድሪባ በማስቆጠር ሰበታዎችን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

በደቂቃዎች ልዩነት ሰበታዎች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ሊያሳድጉበት የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በጫላ ድሪባ አማካኝነት ቢያገኙም ወደ ግብ የላካት ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ልትወጣ ችላለች፡፡ ደሴ ከተማዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል በተለይም በ50ኛው እና በ70ኛው ደቂቃ በድሩ ኑርሁሴን ያደረጋቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ሰበታዎች በመጨረሻው 15 ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቢቀርም መሪነታቸውን አስጠብቀው 1-0 አሸንፈው ወጥተዋል። በዚህም ሰበታ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 47 ከፍ በማድረግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት 180 ደቂቃዎች ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-1 ለገጣፎ ለገዳዲ
(ዮናታን ሙሉጌታ)

09፡00 ላይ ጎፋ በሚገኘው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ የተከናወነው ጨዋታ መልካም ፉክክር የተደረገበት ነበር። ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ለገጣፎዎች በሰነዘሩት ፈጣን ጥቃት በኤሌክትሪክ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው የመሀል አጥቂው ሳዲቅ ተማም ወደ ኋላ ያስቀራትን ኳስ ሀብታሙ ፈቀደ አክርሮ ሲመታ ኳስ በዮሃንስ በዛብህ ጥረት መዳን ሳችል የግቡን መስመር በማለፏ እንግዶቹ ቀዳሚ ሆነዋል። በጊዜ ግብ ያስተናገዱት ኤሌክትሪኮች የመጀመሪያውን አጋማሽ አብዛኛው ደቂቃዎች በተጋጣሚያቸው ሜዳ አሳልፈዋል። ሆኖም በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ሳጥን ይገቡ የነበሩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ሲሆኑ አልፎ አልፎ ከሦስቱ የመሀል ተከላካዮቻቸው ለታፈሰ ተስፋዬ እና ወንድምአገኝ አብሬ የሚያሻግሯቸው ኳሶችም እምብዛም ውጤታማ አልነበሩም። ከዛ ይልቅ ቡድኑ ከቆሙ ኳሶች የተሻሉ ሙከራዎችን አድርጓል። 29ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ከግራው የሳጥኑ ጠርዝ በቀጥታ የመታው የቅጣት ምት በግብ ጠባቂው ጥረት ሲድን 40ኛው ደቂቃ ላይም ከዛው አቅጣጫ ያሻማውን ቅጣት ምት ወልደአማኑኤል ጌቱ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ በመቆየት ተጋጠሚያቸው መሀል ለመሀል የሚሰነዝራቸውን ጥቃቶች በመመከት የተሳካላቸው ለገጣፎዎች ጥቂት የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን አግኝተዋል። ከነዚህም ውስጥ 22ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ተማም እና ዳዊት ቀለመወርቅ በግራ መስመር በፈጠሩት ቅብብል ወደ ሳጥን ደረሰው ዳዊት የሞከረውን ኳስ ዮሀንስ በዛብህ ያዳነበት ይጠቀሳል። ከዚህ ባለፈ ግን መሀል ላይ የቁጥር ብልጫ የተወሰደበት አማካይ ክፍላቸው ለሦስትዮሽ የፊት ጥምረቱ ሌሎች የግብ ዕድሎችን ሳይፈጥር የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች ሙሉ ለሙሉ አጥቅተው የተጫወቱ ሲሆን ለገጣፎዎች ደግሞ መሪነታቸውን በማስጠበቁ ላይ ትኩረት አድርገዋል። እንደመጀመሪያው ሁሉ አሁንም ብልጫ ቢወስዱም የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የተሳናቸው ኤሌክትሪኮች 64ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። የግራ መስመር ተመላላሹ አቡበከር ከሚል ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ወንድምአገኝ አብሬ ከጥቂት ሜትሮች ርቀት ከተከላካዮች ጋር ታግሎ አከታትሎ ሁለቴ በሞከረበት በዚሁ አጋጣሚ ባለሜዳዎቹ በእጅጉ ለጎል ቢቀርቡም አንተነህ ሀብቴ የሚቀመስ አልሆነም። የአጥቂ አማካያዮቻቸው ሽመክት ግርማ እና መክብብ ወልዴን በብሩክ መርጋ እና ዘካሪያስ ከበደ የተኩት ለገጣፎዎች የኤሌክትሪክን ጥቃት በመመከት ቢሳካላቸውም ወደ ግብ የቀረቡት በጥቂት አጋጣሚዎች ነበር። በሳዲቅ ተማም ፍጥነት በመጠቀም ከባለሜዳዎቹ የኋላ ክፍል ጀርባ ወደነበረውን ሰፊ ክፍተት ለመግባት የሞከሩበትም ሂደት ሙከራዎችን አላስመለከተንም። ሀብታሙ መንገሻን በማስገባት የአጥቂዎቻቸውን ቁጥር ሦስት ያደረሱት ኤሌክትሪኮችም ነዋነኛነት ከአማካዩ ሚካኤል በየነ እንቅስቃሴ መነሻነት ተጭነው ቢጫወቱም አቻ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። በመጨረሻ ደቅቃ ከቅጣት ምት በተነሳ እና በተጨራረፈ ኳስ በጌትነት ደጀኔ እና ብሩክ መርጋ አማካይነት ሙከራ ማድረግ የቻሉት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ግን ግብ ባያስቆጥሩም መሪነታቸውን አስጠብቀው ጨዋታውን 1-0 ማሸነፍ ችለዋል። በውጤቱም ከምድቡ መሪ ሰበታ ከተማ ጋር ያላቸውን የአራት ነጥብ ልዩነት አስጠብቀው ለሣምንቱ ወሳኝ ፍልሚያ የሚረዳውን ድል ማሳካት ችለዋል።

አውስኮድ 0-0 ገላን ከተማ
(ሚካኤል ለገሰ)

ቀዝቀዝ ባለ ፉክክር የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጅማሮ የጠራ የግብ እድሎችን ባያስመለክትም ቀስ በቀስ እየተሟሟቀ ሄዷል። ጨዋታው እንደ ተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ በዮናስ ግርማ አማካኝነት ግብ ያስቆጠሩት አውስኮዶች የእለቱ የመስመር ዳኛ ከጨዋታ ውጪ በማለቱ ግቡ ተሽሮባቸው ቅሬታ ቢያነሱም ግቡ ሳይፀድቅ ቀርቶ ጨዋታው ቀጥሏል። ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ጨዋታውን በራሳቸው ቅኝት ለመቃኘት ያሰቡ የሚመስሉት ተጋባዦቹ ገላኖች በ10ኛው ደቂቃ ሚኪያስ አለማየሁ በግል ጥረቱ ከመስመር እየገፋ ሄዶ በሞከረው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበረ። በሁለት ረጃጅም አጥቂዎች ሲጫወቱ የነበሩት አውስኮዶች በበኩላቸው የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም በተደጋጋሚ ወደ ገላኖች የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ሰንዝረዋል። በዚህም በ16ኛው እና በ28ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ ጌታቸው ካሳሁን ባሻማቸው እና ሚካኤል ጆርጅ በሞከራቸው ሁለት ሙከራዎች ለግብ ቀርበው ነበረ።

ገላኖች በተቃራኒው በ26ኛው ደቂቃ ኳስ ከግብ ክልላቸው ጀምረው በመጫወት ጥሩ መኩራ በአብዱረህማን ሙስጠፋ አማካኝነት አድርገው መክኖባቸዋል። እየተሟሟቀ የቀጠለው ጨዋታው ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ብርቱ ፉክክር አስተናግዷል። በ32ኛው ደቂቃ የገላን ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ጥሩ ኳስ ያገኘው ሰዒድ ሠጠኝ አክርሮ መቶ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ሰብረው መግባት የተሳናቸው አውስኮዶች በሐቁምንይሁን ገዛኸኝ ሌላ የርቀት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ወቶባቸዋል። በ43ኛው እና በ45ኛው ደቂቃ ከተመሳሳይ ቦታ የቅጣት ምት ያገኙት ባለሜዳዎቹ አጋጣሚውን በሚካኤል አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት ዳግም ጥሩ እድል ያገኙት አውስኮዶች እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል የሚያመሩበትን እድል በአለሙ ብርሃኑ አማካኝነት ፈጥረው መክኖባቸዋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዞ የጀመረው ጨዋታው ሙከራ ለማስተናገድ 15 ደቂቃዎች ፈጅተውበታል። በ60ኛው ደቂቃ ተደራጅተው ወደ ገላኖች የግብ ክልል የደረሱት የእንዳወቅ አጥናፉ ተጨዋቾች በዮናስ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ በማድረግ የገላኖችን ግብ ፈትሸዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ ኳስ ለተጋጣሚ ሰተው ጨዋታቸውን ማድረግ የቀጠሉት ገላኖች ከየአቅጣጫው ጥቃቶች ሲሰነዘርባቸው ታይቷል። ዮናስ ሙከራ ካደረገ ከሁለት ደቂቃ በኋላም በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ገላን የግብ ክልል ያመሩት አውስኮዶች በታሪኩ ሳጀሌ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል።

ገላኖች ምንም እንኳን ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ቢከላከሉም በአንድ አንድ አጋጣሚዎች ፍጥነት የታከለበት ሽግግር በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህም በ63ኛው ደቂቃ አውስኮዶች ትተውት የሄዱትን ሜዳ በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ሙከራ በአብዱረህማን አማካኝነት አድረገው ግብ ጠባቂው አምክኖባቸዋል። ጥቃት መሰንዘረቀቸውን የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ በ65፣ 67 እና 73ኛው ደቂቃ ከመስመር ባሻሟቸው ኳሶች ጥሩ ጥሩ እድል ቢፈጥሩም ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው ኤርሚያስ ኃይሌ የፍፁም ቅጥት ምት ክልል ውስጥ ወደ ግብ የመታው ኳስ በእጅ በመነካቱ በ80ኛው ደቂቃ አውስኮዶች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱን የውድድሩ አጋማሽ ላይ ቡድኑን የተቀላቀለው ሚካኤል ጆርጅ መቶት ረጅሙ ግብ ጠባቂ ተመስገን ጮናሬ አምክኖበታል።

በከፍተኛ ሊጉ ለመቆየት ጨዋታውን ማሸነፍ የሚገባቸው አውስኮዶች በራሳቸው በኩል ያለውን እድል በራሳቸው ለመወሰን በቀሪ 10 ደቂቃ በይበልጥ አጥቅተው ተጫውተዋል። እንደ አውስኮድ ባይሆንም መጠነኛ የመውረድ ስጋት ያለባቸው ተጋባዦቹ ገላኖች በ85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው እሸቱ ጌታሁን አማካኝነት በሞከሩት ጥሩ ሙከራ ደረጃቸውን የሚያሻሽል ሶስት ነጥብ ለማግኘት ጥረዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ግብ ያመሩት አውስኮዶች ኤርሚያስ ለዮናስ አቀብሎት ዮናስ ሳይጠቀምበት በቀረው አስቆጪ እድል ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት የመጨረሻ እድል ያገኙት ባለሜዳዎቹ ያገኙትን አጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምቱን ባመከነው ሚካኤል አማካኝነት ሞክረውት ወደ ውጪ ወቶባቸዋል። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 መጠናቀቁን ተከትሎ በሁለተኛ ዙር ጥሩ መሻሻል ያሳየው አውስኮድ በሊጉ የመትረፉ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

በሌሎች በዚህ ምድብ በተደረጉ ጨዋታዎች ፌዴራል ፖሊስ ወልዲያን በኃይለየሱስ፣ እንዳለማው ታደሰ እና ሰይፈ ዘኪር ጎሎች 3ለ1 ሲረታ አክሱም ከተማ ወሎ ኮምቦልቻን 2ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ቡራዩ ከተማ ደግሞ ከሜዳው ውጪ አቃቂ ቃሊቲን 2ለ0 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡