ከፍተኛ ሊግ ለ | ወልቂጤ ከተማ ወሳኝ የሜዳ ውጪ ድል ሲያስመዘግብ የዲላ እና መድን ጨዋታ ተቋርጧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ ወልቂጤ ከተማ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ መንገዱን የጠረገበትን ድል ሀምበሪቾ ላይ አሳክቷል። የዲላ እና መድን ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ሲቋረጥ የወራጅ ቀጠናውን ፉክክር ያስቀጠሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ወደ ዱራሜ የተጓዘው ወልቂጤ ከተማ ሀምበሪቾን 1-0 አሸንፏል። በፌዴራል ዳኛ ዓለማየሁ ለገሰ ጥሩ ብቃት የተመራው ይህ ጨዋታ ግብ ለማስተናገድ ደቂቃዎችን አልወሰደም። 1ኛው ደቂቃ ከወልቂጤ የግብ ክልል በረጅሙ የተሻገረችውን ኳስ አህመድ ሁሴን የተከላካዮችን ስህተት እና የግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ መዘናጋት በሚገባ በመጠቀም ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።

በሀምበሪቾ በኩል ኳስን ይዞ ለመጫወት ቢያስቡም ቅብብሎቻቸው ስኬታማ ስላልነበሩ ሶስተኛ የማጥቃት ክፍላቸው ላይ ይቆረጥባቸው ስለነበር ጫና ከመፍጠር ተገድበዋል። እንግዳዎቹ ደግሞ የፊት አጥቂያቸውን አህመድ ሁሴንን ያተኮረ ረጃጅም ኳሶችን ሲጫወቱ ተስተውለዋል። በግራ መስመር ጥሩ እንቅስቃሴን በማድረግ ኳሶችን ወደ ሳጥን እየጣሉ የተቃራኒ ተከላካይ ክፍል ሲረብሽ የነበሩት ባለሜዳዎቹ የአጥቂዎቻቸው የንቃት ጉድለት እንጂ የወልቂጤ ተከላካዮች ጉልህ የሚባል ስህተቶችን መጠቀም ይችሉ ነበር። 4ኛው ደቂቃ መቆያ አልታዬ ክግራ መስመር ወደ ሳጥኑ ያሻማትን ኳስ ተስፋሁን ተሰማ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በአግዳሚው የወጣችበት ለግብ የተቃረበች ሙከራ ነበረች። ጨዋታው በቀጣይ 30 ደቂቃ ውስጥ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴን ያላስመለከተን ሲሆን 34ኛው ደቂቃ ላይ በወልቂጤ ተከላካዮች ስትመለስ ያገኛትን ኳስ ምኞት ማርቆስ በጭንቅላቱ ገጭቶ ኢኖህ ቤሊንጊ ለጥቂት ያወጣበት እና ከቅጣት ምት ዮናስ ታዬ ያሻማትን ኳስ ብርሀኑ አዳሙ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት በሀምበሪቾዎች በኩል እጅጉኑ ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በመጀመሪያው ግማሽ ሁለተኛ ሙከራቸውን ያደረጉት ክትፎዎቹ ኢኖህ ቤሊንጊ የለጋትን አህመድ ሁሴን ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥን ሰብሮ ገብቶ አገባው ሲባል በአግዳሚው ወጥታበታለች። በወልቂጤ 1-0 መሪነት ወደ እረፍት ወጥተዋል። በእረፍት ስአትም የሀምበሪቾው አሰልጣኝ ዓለማየሁ ዓባይነህ ከደጋፊ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን ከደጋፊዎች ጋርም እሰጣ ገባ ውስጥ ገብቶ ተመልክተነዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀምበሪቾ እጅግ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን ወልቂጤዎች ግን የተከላካይ መስመራቸውን ጠጣር በማድረግ በረጃጅም ኳሶች ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። 47ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ መሬት ለመሬት አክርሮ የመታት ጠንካራ ኳስ በርካት ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማምከን የቻለው ኢኖህ ቤሊንጌ ተወርውሮ እንደምንም ያወጣበት የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች። የወልቂጤን ተከላካዮች በሁለተኛው ግማሽ ሲያስጨንቅ የነበረው ዘካርያስ ፍቅሬ ሁለት ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። 67ኛው ደቂቃ ከዮናስ ታዬ ባገኛት ኳስ ሞክሮ ቤሊንጊ ያዳነበት እና መቆያ አልታዬ ኳስ ከሚጀመርበት መሀል ሜዳ ያሻገራትን ኳስ በደረቱ አብርዶ ተቀልብሶ ሞክሮ በአግዳሚው ለጥቂት የወጣችበት የሚጠቀሱ ናቸው።

82ኛው ደቂቃ ላይ የሀምበሪቾ ደጋፊዎች በራሳቸው ተጫዋቾች ላይ ባነሱት ቅሬታ ወደ መጫወቻ ሜዳ፣ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች እንዲሁም በሁለቱም ክለቦች ተቀያሪ ወንበር ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ደንጋይ በመወርወራቸው ጨዋታው ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ተቋርጦ በፖሊስ ከፍተኛ ርብርብ ተረጋግቶ ጨዋታው የቀጠለ ሲሆን ተጨማሪ ጎሎች ሳይሰተናገዱበት በወልቂጤ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አባላት እና የወልቂጤ ደጋፊዎች ከስታዲየም ውጭ የነበረው ግርግር እስኪረግብ ለረጅም ስዓታት በስታዲየም እንዲቆዩ ተደርጓል።

በተመሳሳይ ሰዓት ወደ ዲላ ተጉዞ ላለመውረድ እየተጫወተ የሚገኘው ዲላ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን እስከ እረፍት 2-0 እየተመራ ጨዋታው በዝናብ ምክንያት ተቋርጧል። ዲላ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ሄኖክ ተረፈ እና ፋሲል አበባየሁ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 እየመሩ ወደ እረፍት ቢያመሩም ሁለተኛው አጋማሽ ሊጀመር ሲል በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በዳኞች እና የክለቦች መሪዎች ስምምነት ወደ ነገ 4፡00 ዞሯል።

በለሎች ጨዋታዎች ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ በአቡሽ ደርቤ እና ኤፍሬም ቶማስ ጎሎች ወላይታ ሶዶ ከተማን 2-1 ሲያሸንፍ አአ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማ ኢኮስኮን 1-0 ረቷል። .

ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ናሽናል ሴሜንት እና የካ ክፍለ ከተማ ረፋድ ላይ ባደረጉት ጨዋታ 1-1 ሲለያዩ ግርጌ ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ፖሊስ ነገሌ አርሲን 3-2 አሸንፎ ላለመውረድ ትግሉን ቀጥሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡