የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ

በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቶ ሁለት ሳምንታት እና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የቀረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለፉት ሳምንታት ውዝግብ አሁንም ሲቀጥል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ29ኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች ነገ በተያዘላቸው መርሐ ግብር ይካሄዳሉ ብሏል።

ነገ ከሚደረጉ ጨዋታዎች ቅድሚያ እንደሚደረግ መርሐ ግብር የወጣለት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ስሑል ሽረ ነው። ጨዋታው 4:00 ላይ በትግራይ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን 9:00 ላይ የደደቢት እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ የሚካሄድ በመሆኑ ቀደም ብሎ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ፋሲል ከነማ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው)፣:መቐለ 70 እንደርታ (ከሜዳው ውጪ) እና ሲዳማ ቡና ከ ደደቢት (ከሜዳው ውጪ) በተመሳሳይ 9:00 የሚጫወቱ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ ጋር ያለውን ተሰካካይ ጨዋታ ሳያከናውን ከፋሲል ጋር እንደማይጫወት በጋዜጣዊ መግለጫ በማስታወቅ ወደ ስፍራው አልተጓዘም። መቐለ እና ሲዳማም በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ቢገልፁም ፌዴሬሽኑ ጨዋታዎቹ በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት እንደሚደረጉ አስታውቋል።

ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር፣ ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ ሌሎች በነገው ዕለት በተመሳሳይ 9:00 የሚደረጉ የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡