ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀድሞ አሰልጣኙን ለሦስተኛ ጊዜ ለመቅጠር ተቃርቧል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ በትናትናው ዕለት በቅሎ ቤት በሚገኘው የክለቡ ፅህፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል።

በመግለጫው ላይ ከሚዲያ አካላት እግረ መንገድ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የክለቡ ቀጣይ አሰልጣኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ በስፋት እየተነገረ በሚገኘው ሚቾ ዙርያ ክለቡ ያለው ምላሽ ምንድነው? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ አቶ ሰለሞን በቀለ ይህን ተናግረዋል።

“የሰሞኑን የኢንተርኔት መቋረጥ ነው እንጂ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ለክለባችን አሰልጣኝ እንሁን ብለው ያመለከቱ አሰልጣኞች ብዛት ከፍተኛ ነው። በመመረጣችን እጅግ ደስ ይለናል። ማን ይሁን አሰልጣኙ የሚለው ጉዳይ ግን ወደ ፊት እንነግራችኃለን። ሆኖም ግን የምናሰናብታቸው ተጫዋቾች አሉ፣ የምንቀበላቸውም ተጫዋቾች አሉ። ከዚህ አስቀድሞ ግን የአሰልጣኙን ሁኔታ ማወቅ እና መወሰን አለብን። እንደ ዓምና እና ካቻምና አይነት ስህተት ውስጥ አንገባም። ይህን ላረጋግጥላቹ እወዳለው። ቀደም ብለን አሰልጣኙ ማን መሆን እንዳለበት እንወስናለን። መልካም አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል በዛ መሠረት እንሄዳለን” ብለዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮቿ ማረጋገጥ እንደቻለችው ከሆነ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” ወደ ቀድሞ ክለባቸው ለሦስተኛ ጊዜ ለመመለስ መስማማታቸውን ለማወቅ ችላለች።

ሚቾ ከዚህ ቀደም ከ1997 እስከ 98 እንዲሁም ከ2000 እስ ከ2002 በፈረሰኞቹ በቆዩባቸው አምስት የውድድር ዓመታት በሁሉም የሊግ ዋንጫ ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: Content is protected !!