የአሰልጣኞች አስተያየት| መከላከያ 1-2 መቀለ 70 እንደርታ

ዛሬ ከተካሄዱ የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በአዲስ አበባ ስታድየም መቐለ 70 እንደርታ መከላከያን 2-1 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

“ወደ ዋንጫ እየተራመድን እንደመገኘታችን ጨዋታውን በጥንቃቄ ነበር የተጫወትነው”-ገብረመድህን ሀይሌ(መቀለ 70 እንደርታ)

ስለ ጨዋታው

“በዛሬው ጨዋታ የተጫዋቾቼ የመጫወት ፍላጎት እና ስሜት ጥሩ ነበር፤ ወደ ዋንጫ እየተራመድን እንደመገኘታችን ጨዋታውን በጥንቃቄ ነበር የተጫወትነው። እንደአጠቃላይ እንቅስቃሴያችን ጥሩ ነበር፡፡”

ስለ ሥዩም ተስፋዬ ቀይ ካርድ

“የሊጉ የዳኝነት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው። እኛ በተደጋጋሚ የሚሰሩብን በደሎች በጣም በርካታ ናቸው ፤ በዛሬው ጨዋታ እንኳን አራተኛው ዳኛ ከዚህ ጋር ሆኖ ሁኔታውን እንዴት ሊመለከተው እንደቻለ ለእኔ አልገባኝም ፤ ዳኛው በጣም በቅርብ ርቀት ነው የነበረው። ሁሉንም ነገር መቆጣጠር እየቻለ እገዛ መጠየቁ አልገባኝም፡፡”

“የቻልነውን ያክል በሊጉ ለመቆየት ጥረናል ግን አልተሳካም” በለጠ ገ/ኪዳን (መከላከያ)

ስለ ጨዋታው

“በወራጅ ቀጠና ውስጥ እንደመገኘታችን ጨዋታው ከእነሱ ይልቅ ለእኛ ወሳኝ ነበር ፤ እንደቡድን ማድረግ የሚገባንን በሙሉ አድርገናል፡፡ ጨዋታው ከእረፍት በፊት ነበር መጠናቀቅ የነበረበት ስድስት አጋጣሚዎች ፈጥረን መጠቀም ሳንችል ቀርተናል። በአንጻሩ እነሱ ሁለት አግኝተው ሁለቱንም አስቆጥረዋል፡፡በጨዋታው ተጫዋቻችን አሸንፈው ለመውጣት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ነገርግን ይህ ፍላጎት በተለይ የፊት መስመር ተሰላፊዎቻችን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ እንዳይረጋጉ አድርጓቸዋል፡፡ የቻልነውን ያክል በሊጉ ለመቆየት ጥረናል፤ ግን አልተሳካም። በቀጣይ ዓመት ከስህተቶቻችን ተምረን ወደ ሊጉ ለመመለስ እንሰራለን፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡