ሪፖርት | ደቡብ ፖሊስ ወደ ከፍተኛ ሊግ መመለሱን ሲያረጋግጥ ወላይታ ድቻ አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛው ሳምንት ጨዋታ ደቡብ ፓሊስ በሜዳው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1-1 ተለያይቶ በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ተረጋግጧል፡፡ ድቻ ደግሞ በሜዳው አዳማ ከተማን 2-0 አሸንፏል።

ደቡብ ፖሊስ 1-1 ኢትዮጵያ ቡና

ተጠባቂነቱ ከኢትዮጵያ ቡና ይልቅ ለደቡብ ፖሊስ እጅግ ወሳኝ በነበረው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ ወስደው መጫወት ችለው ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃሩ የደቡብ ፖሊሱ አጥቂ የተሻ ግዛው ወደ ራሱ የግብ ክልል ለግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ለመስጠት ሲሞክር አቡበከር ናስር ደርሶባት ግብ ጠባቂው ካስጣለው አጋጣሚ ውጪ የሚጠቀስ ሙከራን ማድረግ ያልቻሉበት ነበር፡፡

በ12ኛው ደቂቃ በቀኝ የግብ አቅጣጫ የተሻ ግዛው ወደ ሳጥን ይዞት የተጠጋውን ኳስ ብሩክ አየለ በቀጥታ ቢመታውም ወንደሰን አሸናፊ ሲያድንበት 23ኛው ደቂቃ ላይ አናጋው ባደግ ከቀኝ ክፍል በቀጥታ ሲመታ የግብ ጠባቂው ወንደሰን አሸናፊ ግቡን ሲሸፍን በመሳሳቱ ኳሷ መረብ ላይ አርፋ ፖሊሶችን መሪ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም ከተከላካይ ክፍል አንስቶ እስከ ፊት መስመሩ ድረስ የተሻሉ የነበሩት ፖሊሶች ቢሆኑም ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ 51ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሳምሶን ጥላሁን ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ አሥራት ቱንጆ በግንባሩ በመግጨት ቡናን አቻ አድርጎል፡፡ ደቡብ ፖሊሶች ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ የተሻ ብቻውን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ብረት የመለሰበት እና ብሩክ ኤልያስ በተደጋጋሚ ያገኛቸው የግብ ዕድሎች ድል ለማስመዝገብ ጥረት ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ጨዋታው 1-1 በመጠናቀቁ ደቡብ ፖሊስ በመጣበት የመጀመሪያው ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ዳግም ተመልሷል፡፡

ወላይታ ድቻ 2-0 አዳማ ከተማ

ሶዶ ላይ የዓመቱ የመጨረሻ የሜዳው ጨዋታውን ያደረገው ወላይታ ድቻ በመጀመርያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ጎሎች አሸንፏል። የመስመር አጥቂው ቸርነት ጉግሳ ገና በ3ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ የቡድኑን አጀማመር ሲያሳምር በ33ኛው ደቂቃ አንጋፋው ተከላካይ ደጉ ደበበ ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡