አዳማ ከተማዎች አሸናፊ በቀለን ለመቅጠር ወስነዋል

አዳማ ከተማዎች የቀድሞ አሰልጣኛቸው አሸናፊ በቀለን በድጋሚ ለመቅጠር ወስነዋል። የአሰልጣኙ ምላሽም ይጠበቃል።

ለቀጣይ ውድድር ዓመት አሰልጣኝ ለመቅጠር ከወዲሁ ስራዎች በመጀመር ከዮሐንስ ሳህሌ፣ ግርማ ሃብተዮሃንስ እና አሸናፊ በቀለ አንዳቸውን አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም እያጤነ የቆየው የአዳማ ከተማ ስራ አስፈፃሚ ባለፈው ዓርብ ባካሄደው ስብሰባ አሸናፊ በቀለ አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም መወሰኑ ታውቋል።

ከዚህ ቀደም ከ2006 እስከ 2009 ድረስ በአዳማ ከተማ ቆይታ የነበራቸውና ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ በማሳደግ በተከታታይ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ የረዱት አሰልጣኙ ወደ ውጤታማነት ይመልሳሉ ተብሎ በክለቡ ታምኖባቸዋል።

አሸናፊ በቀለ ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ ጀምሮ በወላይታ ድቻ እየሰሩ የነበረ ሲሆን ክለቡ ቆይታቸውን ለማራዘም ፍላጎት ያለው በመሆኑ ድርድር ላይ መሆናቸው ታውቋል። ስምምነት ላይ ከደረሱም በወላይታ ድቻ ሊቆዩ እንደሚችሉ ሲጠበቅ ሁኔታዎች በተቃራኒው መንገድ ከተጓዙና ከአዳማ ጋር የሚስማሙ ከሆነ በድጋሚ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው ይሾማሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡