ቻን 2020 | ከጅቡቲ መልስ ሦስት ተጫዋቾች ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ይቀላቀላሉ

በ2020 በካሜሩን ለሚዘጋጀው ቻን ቅድመ ማጣሪያ ከጅቡቲ ጋር ጨዋታ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመጀመሪያው ጨዋታ መልስ ሦስት ተጫዋቾችን ይቀላቅላል፡፡

ሐምሌ 19 ጅቡቲ ላይ ተጫውተው የሚመለሱት ዋልያዎቹ የመልሱን ጨዋታ በአንድ ሳምንት ልዩነት ድሬዳዋ ላይ ያደርጋሉ፡፡ ቡድኑ በአዳማ ከተማ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምድን የጀመረ ቢሆንም በጉዳት እና ፓስፖርት ጉዳዮች በተሟላ ሁኔታ ማድረግ አልቻለም። ሙጂብ ቃሲም ከፓስፖርት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከመጀመሪያው ማጣሪያ ውጪ የሆነ ሲሆን ለመልሱ ግን ዳግም ጥሪ እንደሚደረግለት አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ ገልፀዋል፡፡

አሰልጣኙ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ሶስት ወጣት ተጫዋቾችን ከጅቡቲ መልስ ድሬዳዋ ላይ ለሚደረገው ጨዋታ ጥሪ ይደረግላቸዋል። ከአዳማ ከተማ ተስፋ ቡድን የተገኘው ፉአድ ፈረጃ ለመልሱ ጨዋታ ወደ ቡድኑ የሚቀላቀል ተጫዋች ነው፡፡ አማካዩ በአሁኑ ሰዓት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በአዳማ ተቀላቅሎ ልምድድ እየሰራ ሲሆን ቡድኑ ከጨዋታው ሲመለስ ድሬዳዋ ላይ ይቀላቀላል ተብሏል።


በሀዋሳ ከተማ በመጋቢት ወር ላይ ከተስፋ ቡድን ካደገ በኃላ ባደረጋቸው ስድስት የነጥብ ጨዋታዎች 7 ግቦችን ያስቆጠረው ወጣቱ አጥቂ መስፍን ታፈሰ ቡድኑን ከሚቀላቀሉት አንዱ ነው፡፡ ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ሀዋሳ ከፋሲል ባደረጉት ጨዋታ ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በስፍራው የነበሩት አሰልጣኙም ከተመለከቱት በኃላ ነው ሊጠሩት የቻሉት፡፡

ሌላኛው ጥሪ የሚደረግለት የድሬዳዋ ከተማው የአማካይ እና የመስመር ተጫዋቹ ረመዳን ናስር ነው። ረመዳን በተለይ በሁለተኛው ዙር ድሬዳዋ ከተማ ላሳየው መሻሻል ጎሎች በማስቆጠር እና በግሉ ጥሩ በመንቀሳቀስ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡