ወልዋሎ ሜዳውን ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ብቁ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩንቨርስቲ ጨዋታዎቹን የሚያደርግበት ሜዳ ደረጃን አሻሸሎ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ብቁ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል።

ግንባታውን በተመለከተ የቡድኑ ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ አማረ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሒደቱን አብራርተዋል። ” ሜዳውን በአዲስ መንገድ መስራት ጀምረናል። በቅርቡ ሳር የማንጠፍ ሥራ እንጀምራለን። አሁን ያለበት ደረጃ የበፊቱን አፈር ሙሉ ለሙሉ በማንሳት የአሸዋ እና የለም አፈር ሙሌት ተከናወኗል። በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የሳር ተከላውን እናከናውናለን።


” ከሜዳ ስራው በተጓዳኝ በስታድየሙ አቅራቢያ የውሃ ጉድጉድ ቁፋሮ የሚደረግ ሲሆን ይህም ቁፋሮ ሲያልቅ ለሜዳው የሚሆን በቂ የውሃ አቅርቦት ከዚህ የምናገኝ ይሆናል። በባለፉት ወራት ከሳር ተከላው በፊት መጠናቀቅ ያለባቸው ተፋሰስ ስራዎች ሲገጠሙለት የቆየው ይህ ስቴድየም እኚህን የተፋሰስ እና ተያያዥ ስራዎች አጠናቋል። የተመልካች ወንበሮች ሥራ ከሞላ ጎደል ተጠናቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለብ ላይሰንስ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተድላ አዲግራት ድረስ በመምጣት ግብኝተውታል። ከሳቸውም ጥሩ ምላሽ ነው ያገኘነው። ስለዚህም የሚቀጥለውን ውድድር ዓመት በሜዳችን ነው የምናከናውነው። ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡