ፋሲል ከነማ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ዝግጅታቸውን ነገ ይጀመራሉ

ሀዋሳ ከተማን በመለያ ምቶች በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ያነሳው ፋሲል ከነማ ከታንዛኒያው አዛም ጋር የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ነሐሴ 5 ቀን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ያደርጋል። ጨዋታውን በሚያደርግበት ባህር ዳር ከተማም አዲስ አምባ ሆቴል መቀመጫውን በማድረግ ከነገ ጀምሮ በጂም እና በሜዳ ላይ ልምምዱን ይጀምራል። በቡድኑ ውስጥ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች በቀር ነባር እና አዳዲስ ፈራሚዎች ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ምንም እንኳ ከቡድኑ ጋር ለመለያየት የመልቀቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡ ቢሆንም ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ቡድኑን ለጨዋታው ለማዘጋጀት ባህርዳር ከተማ ገብተዋል። ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገላቸው ያሬድ ባዬ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሙጂብ ቃሲምም ከጅቡቲ ጨዋታ መልስ ቡድኑን የሚቀላቀሉ ይሆናል።

ፋሲል ከነማ የመልሱን ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ከነሐሴ 17-19 ባሉት ቀናት የሚያከናውን ሲሆን ይህን ዙር ካለፈም በመስከረም ወር ከዛምቢያው ትሪያንግልስ እና ከብሩንዲው ቱኪንዞ ጋር ይጫወታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡