ኦኪኪ አፎላቢ ከጅማ ለመልቀቅ ወስኗል

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር ዘንድሮ በበጀት ምክንያት ለተጨዋቾቹ ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ቅሬታቸውን ለፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸው የሚታወስ ሲሆን በዓመቱ አጋማሽ የፈረመው ኦኪኪ አፎላቢም ደሞዝ እንዳልተከፈለው በመግለፅ ከክለቡ ጋር ለመለያየት እንደወሰነ ወኪሉ ገልጿል።

የተጫዋቹ ወኪል ኸሪተጅ ሶከር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ተወካይ የሆነው ሳምሶን ናስሮ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ከሆነ ክለቡ ለደንበኛቸው (ኦኪኪ አፎላቢ) የሦስት ወር ደሞዝ ማለትም 21 ሺ ዶላር እንዳልተከፈለው፤ በዚህም ተጨዋቹ ደስተኛ እንዳልሆነ እንዲሁም ወደ ሃገሩ ናይጄሪያ ሲያመራም ያለ ገንዘብ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ተጨዋቹ ከክለቡ ጋር መቀጠል እንደማይፈልግ በመወሰን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ክለቡ በስምምነት እንዲለቀው ደብዳቤ ማስገባታቸውን አቶ ሳምሶን አስረድተዋል።

ስለ ተጨዋቹ እና ክለቡ ውል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ሳምሶን ውሉ ምንም ተፅዕኖ እንደማያደርግባቸው እንደውም ውሉን ማቋረጥ የፈለገ ወገን ውሉን ሙሉ ለሙሉ በስምምነት ማቋረጥ የሚያስችል አንቀፅ እንዳለው ተናግረዋል። ከፌዴሬሽኑ ምላሽ እስከሚሰጣቸው ድረስ እንደሚጠብቁ የተናገሩት ወኪሉ በቀጣይ የሚፈልጉት ምላሽ ካልተሰጣቸው ወደ ካፍ እና ፊፋ ጉዳዩን እንደሚወስዱት ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙርያ የጅማ አባጅፋርን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን ምላሽ ካገኘን የምንገልፅ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡