ድሬዳዋ ከተማ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗል

ድሬዳዋ ከተማ ባሰናበታቸው ተጫዋቾች ዙርያ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በመጋቢት ወር መጀመሪያ አጥቂዎቹ ዮናታን ከበደ እና ኃይሌ እሸቱ እንዲሁም ተከላካዩ ወሰኑ ማዜን ከክለቡ ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም የተሰናበቱት ሦስቱም ተጫዋቾች ቀሪ የስድስት ወራት የውል ኮንትራት እያለን ያለ አግባብ ተሰናብተናል በሚል ቅሬታ ማሰማታቸውን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ተጫዋቾቹ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ነው በማለት በ10 ቀን ውስጥ ለተጫዋቾቹ ደሞዛቸው እንዲከፈል የሚል የውሳኔ ደብዳቤን ለክለቡ ቢልክም ክለቡ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ውሳኔው አግባብነት እንደሌለው ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም የክለቡ ጥያቄ በድጋሚ ውድቅ በመደረጉ ለሁለተኛ ጊዜ ፌዴሬሽኑ ለድሬዳዋ ማስጠንቀቂያ አዘል ደብዳቤን በድጋሚ ከላከ በኋላ ተፈፃሚ ባለማድረጉ ምክንያት የዲሲፕሊን ኮሚቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ አግዶ ቆይቷል፡፡ የክለቡ ቦርድ በስተመጨረሻም ተጫዋቾቹ የጠየቁት ለሁለት ተጫዋቾች የሦስት፣ ለአንድ ተጫዋች ደግሞ የአንድ ወር ደሞዝ ለመክፈል መዘጋጀቱን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበስ አውግቸው በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ “እንዲከፈላቸው ተወስኗል። በሊግ ኮሚቴው ውሳኔው መሠረት ዞሮ ዞሮ እልህ መጋባት ስለሌለብን በሚል ነው። ነገር ግን ውሳኔው ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት። የህዝብ ክለብ እንደመሆኑ መጠን ክርክር አያስፈልግም፤ በቃ የተባልነውን ውሳኔ ተግባራዊ አድርገን እገዳው እንዲነሳ እንጠይቃለን።” ብለዋል፡፡

በእናንተ በኩል ክፍተት ነበር ወይ ብለን ለጠየቅናቸው ስራ አስኪያጁ ሲመልሱ “ክፍተት በኛ በኩል ምንም የለም ብለን ነው የምናስበው። ለምሳሌ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በ25 ደብዳቤ ፅፎ በ26 ድረስ ምላሽ ስጡበት የሚልበት አግባብ ይህን ሁኔታ ይገልፀዋል፡፡ እንደዛም አድርገን የእነሱ ደግሞ ውሳኔው ሁለት ወር ከሁለት ቀን በኃላ ዘግይቶ የመጣበት ሂደት ነው ያለው፤ ይሄ በራሱ የሚጋጭ ነው። ለምን በጊዜ አልተወሰነም? ብዙ ክፍተት አለ፤ የተጠየቅነው ሌላ የተፈረደብን ሌላ.. ምላሽ ስጡ የሚል ጥያቄ ተጠይቀን የተወሰነብን ደግሞ ሌላ ነው።

” እኛ ጋር በሙሉ ክፍተት የለም ማለትም ይከብዳል፡፡ እኛ ጋር ክፍተት ቢኖርም ግን የዲሲፕሊን ኮሚቴው እየሄደበት ያለው አካሄድ በሙሉ ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። በእርግጥ የተለያዩት ተጫዋቾች ውል ይቀራቸዋል፤ አቋማቸው ጥሩ ካልሆነ ግን ተሸክመን መጓዝ አንችልም በሚል ነው የተለያየነው፡፡ በመጨረሻ ቦርዱ ውሳኔን አሳልፏል። ክለቡ ታግዶ ይሄን ያህል መቆየት ስለሌለበት ደመወዛቸው ይከፈላቸው የሚል ውሳኔም ተላልፏል። ይህን ተፈፃሚ ለማድረግ ዝግጅት ጀምረናል። ደመወዛቸውን ከፍለን እገዳው እንዲነሳ ፌዴሬሽኑን እንጠይቃለን።” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡