ሦስቱ ክለቦች ወደ ዱባይ ስለሚያደርጉት ጉዞ መግለጫ ተሰጠ

በኢትዮ አል-ነጃሺ የጉዞ ወኪል እና በትግራይ እግርኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት ስለተዘጋጀው የቅድመ ውድድር ዝግጅት መግለጫ ተሰጠ።

ከሳምንታት በፊት ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ዱባይ እንደሚያመሩ መግለፃችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ከኦገስት 25 – ሴፕቴምበር 4 ስለሚቆየው ቅድመ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች በኖብል ሃውስ ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል። የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንገሶም ካሕሳይ፣ የኢትዮ ነጃሺ ተወካይ አቶ ያሲን ራጅኡ እና የወልዋሎ ስራ አስከያጅ አቶ አሸናፊ አማረ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በርካታ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ከእግር ኳስ ክለቦቹ በተጨማሪ ደጋፊዎች ወደ ስፍራው እንዲያቀኑ ሁኔታዎች እንደተመቻቹ እና ለዛም የሚረዱ ፓኬጆች እንዳሉ ተገልፅዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ሃሳብ በመስጠት ቀዳሚ የነበሩት አቶ ያሲን ራጅኡ ሲሆኑ ድርጅታቸው በቱሪዝሙ ዘርፍ የሰራው ስራ ከእግር ኳሱ ጋር በጋራ በመሆንም ለመድገም እንዳሰቡ ገልፀዋል።
” ጉዞው ከአምስት ወራት በፊት ቀድሞ የታሰበ ነበር፤ መቐለ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ ለትግራይ እግር ኳስ ጥሩ መነቃቃት ይፈጥራል። ” ያሉት አቶ ያሲን እግር ኳስ እና ቱሪዝም የተያያዙ መሆኑን ገልፀው ይህንን ለመጠቀም ሰፊ ስራዎች እንደታሰቡ በስፋት ገልፀዋል።

“ጉዞው ከእግር ኳስ ውጭ ብዙ ዓላማዎች አሉት።” ያሉት አቶ ያሲን ድርጅታቸው በትምህርት ዘርፍም ትልቅ ፕሮጀክት ቀርፆ ለማሳካት ጥረት ላይ እንዳለ በሰፊው ገልፀዋል።

ቀጥለው ሃሳባቸው የሰጡት የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አንገሶም ካሕሳይ ሲሆኑ ጉዞው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀው እግረ መንገዳቸውንም ፌዴሬሽናቸው ለኤርትራ ክለቦች የእንጫወት ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት እንዳጣ ተደርጎ እየተወራ ያለው ወሬ ሃሰት እንደሆነ ገልፀዋል። ከጉዞው በፊት ከሃገሪቱ ትላልቅ ክለቦች ጋር በታዳጊዎች እግር ኳስ ዙርያ ለመነጋገር እንዳሰቡ የገለፁት አቶ አንገሶም ውድድሩ ለክለቦቹ ያለው ጠቀሜታም ገልፀዋል።

በመጨረሻ ሃሳባቸው የገለፁት ከተሳታፊ ክለቦች በብቸኝነት የተገኙት የወልዋሎው ስራ አስከያጅ አቶ አሸናፊ አማረ ሲሆኑ ጉዞው ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀው ቡድናቸው ወልዋሎ ለቅድመ ውድድር ዝግጅቱ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡