ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ሰባት – ክፍል አንድ

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም 25ኛ ሳምንት መሰናዶ ወደ ገናናዋ ብራዚል ይወስደናል። 


ዓመታዊው ክብረ በዓል እና እግርኳስ

በ1956 የቤላ ጉትማን እና <ኻኖቭድ> ክለብ መዳረሻ የነበረችው ብራዚል የእግርኳሷ ገጽታ ሃንጋሪያዊው አሰልጣኝ በጥልቀት ሊያስተካክለው ካቀደው ታክቲካዊ ኋላቀርነት እጅጉን የራቀ ነበር፡፡ በእርግጥ በደቡብ አሜሪካዋ ሃገር የተናጠል ቴክኒካዊ ክህሎት (Individual Technique) እና ቅድመ ዝግጅት ያልተደረገባቸው በደመነፍስ የሚከወኑ እግርኳሳዊ እንቅስቃሴዎች (Improvisation) ተወዳጅነት ነበራቸው፡፡ ከሌሎች ፎርሜሽኖች በተለየ W-M በብራዚል ቀደም ብሎ ቢታወቅም ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የሚኖራቸውን ነጻነት ስለሚገድብ እና የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን በጥብቅ ክትትል ስር ለማቆየት አመቺ መዋቅር ስለሚፈጥር በቀላሉ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ይህ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ግትር ከመሆኑ አንጻር የሃገሬው ህዝብ ሊያይ የሚሻውን ተሰጥኦና የግል ፈጠራ (Self-Expression) እንዲመለከቱ አልፈቀደላቸውም፡፡ ስለዚህ 4-2-4 በመላ ሃገሪቱ እግርኳስ የመለመድ እድልና ቅቡልነት አገኘ፡፡

የብራዚሎች እግርኳስ አጀማመር አፈ-ታሪክ ተዓማኒነት ካለው እና መነሻው ላይ የሚስተዋሉ ጥርጣሬዎች መጠነኛ የእውነታ ማስረጃ ከተገኘላቸው ስፖርቱ በሃገሪቱ የደረሰው በቻርለስ ሚለር አማካኝነት እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ ከእንግሊዛዊ አባትና ብራዚላዊት እናት በሳኦፖሎ የተወለደው ሚለር የተሻለ ትምህርት እንዲያገኝ ተብሎ ወደ እንግሊዝ ተላከ፡፡ ወላጆቹ በደማቋ የብራዚል ከተማ በቡና ንግድ ላይ ከተሰማሩት ቁንጮ ሸሪኮች መካከል ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ ሚለር በእንግሊዝ የትምህርት ቤት ቆይታው ስለ ጨዋታው ብዙ ተማረ፤ በተጫዋችነት ሃምሻየርን የመወከል አጋጣሚም ተፈጠረለት፤ በአካባቢው ከሳውዛምፕተን በፊት ለተመሰረተው ሴይንት ሜሪ ቡድንም አያሌ ጨዋታዎችን አደረገ፡፡ ቻርለስ ሚለር በ1894 ወደ ሳኦፖሎ ሲመለስ ሁለት ኳሶችን ይዞ መጣ፤ ሁለቱንም በእያንዳንዱ እጆቹ ይዞ አባቱ ፊት ቀረበ።

” ቻርለስ! ደ’ሞ ምንድን ነው የያዝከው?” አባትየው መጠየቅ ነበረበት፡፡

” ዲግሪዎቼ ናቸው፡፡” ቻርለስ መለሰ፡፡

” ልጅህ በእግርኳስ ተመርቋል፡፡” ሲልም አከለ፡፡

የታሪኩ ጥቃቅን ዝርዝሮች በአመዛኙ እውነት ላይሆኑ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ እንዲሁ ተቀባይነት እንደማያገኙ መገመት አያስቸግርም፡፡ እግርኳስ በብራዚል ገና ከጅምሩ የሃሴት ምንጭ፣ አስፈጋጊ፣ አስገራሚ፣ ወጥነት የተላበሰ ሥርዓት ለማስያዝ የማይመች እና ሌሎችም ያልተለመዱ ባህርያት ነበሩት፡፡

ስፖርቱ በብራዚል ውስጥ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ብሪታኒያዊ ዜግነት ባላቸውና በሃገሬው ተወላጆች ዘንድ በፍጥነት መስፋፋት ጀመረ፡፡ በ1902 በሳኦፖሎ ተስፋ ሰጪና አዳጊ የሊግ ፕሮግራም ተጀምሮ ነበር፡፡ በሲውዘርላንድ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ ከእግርኳስ ጋር የተዋወቀው ሌላው አንግሎ-ብራዚላዊ ኦስካር ኮክስ ደግሞ ጨዋታው በሪዮ ዲ ጂኔይሮ እንዲለመድ የራሱን ጥረት አደረገ፡፡ ኮክስ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ፍሎሚኔንሴ የተሰኘውን ዝነኛ ክለብ ለመመስረት በቃ፡፡ እንደ ቀደምቶቹ የደችና ዴንማርክ ክለቦች ሁሉ ፍሎሚኔንሴም ከፍተኛ የብሪታኒያ እግርኳስ ተጽዕኖ አረፈበት፤ የቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴም ግልጽ በሆነ መልኩ በእንግሊዞቹ የአጨዋወት ስልት የተቃኘ ሆነ፡፡ ተጫዋቾቹ ከአፍንጫቸው ሥር የሚገኘው የጺም አቆራረጥ፣ የባርኔጣ አጣጣላቸው፣ የድል ደስታ አገላለጻቸውና ወኔያምነታቸው ሳይቀር ከእግርኳስ ጀማሪዋ ሃገር በቀጥታ የተቀዳ ነበር፡፡ ሚለርም ቢሆን የጥንቱን የስኮትላንዶች <ድሪብሊንግ> (Old-School Dribbling) ዘይቤ አድናቂ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሃገራቸው ርቀው በተለያዩ አህጉራት በሚኖሩ እንግሊዛውያን እንዲሁም እዚያው ብሪታኒያ ምድር ባሉ የሃገሬው ሰዎች ዘንድ የጨዋታው አቀራረብ መንገድ ሊመሳሰል የማይችልበት አንዳች ምክንያት አልነበረም፡፡

በሁሉም ቦታ እንደሆነው ሁሉ በአንግሎ-ብራዚላውያን ጥረት በተቋቋሙ ክለቦች ውስጥ <ድሪብሊንግ> ቀስ በቀስ ቅብብሎች ላይ በተመሰረተው ጨዋታ (Passing Game) እየተተካ ሄደ፡፡ ምንም እንኳ ቀደም ባሉት ጊዜያት በጂሚ ሆጋን እና ብራዚል መካከል የታየው ግንኙነት ልል የነበረ ቢሆንም በሃሪ ብራድሾው ውሳኔ በፉልሃም ክለብ በማሰልጠን ካሳለፉት ስኮትላንዳውያን አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆነው ጆክ ሃሚልተን በ<ሲ.ኤ. ፓውሊስታኖ> ተቀጠረ፡፡ ሥራውን እንደጀመረም “የሃገሪቱ እግርኳስ እድገት ከጠበቅሁት በላይ ሆኖብኛል፤የላቀው የተጫዋቾቹ ህብር ደግሞ እጅጉን አስገርሞኛል፡፡” ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፡፡ ከስኮትላንድ ተሰደው መቀመጫቸውን በሳኦፖሎ ባደረጉ ሰፋሪዎች በ1912 ለተቋቋመው <ስኮቲሽ ዎንደረርስ> ቡድን አዎንታዊ ተጽዕኖ ምስጋና ይግባና የጊዜው ተጫዋቾች ይበልጡን ችሎታቸው ያድግ ጀመር፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ውስብስብ ባሉ መስመሮች የሚከወኑ ተከታታይ ቅብብሎችን የያዘ አጨዋወት (Pattern- Weaving Approach) ይለማመዳሉ፤ ስልቱንም “ሲስተማ ኢንጀሊዛ/ Systema Ingeliza/ (English System)” እያሉ ይጠሩት ነበር፡፡

በስኮትላንድ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሁለት የውድድር ዘመናትን በ<ኧዩር ዩናይትድ > ያሳለፈው የዋንደረርሶች ስመጥር ተጫዋች የግራ መስመር ተሰላፊው አርቺ ማክሊን ነበር፡፡ ቶማስ ማዞኒ በ1950 ባሳተመው <የብራዚል እግርኳስ ታሪክ> መጽሃፉ ላይ እንደጠቀሰው ” ማክሊን የስኮትላንዶችን አጨዋወት በአግባቡ ሊወክል የሚችል ጥበበኛ ተጫዋች ነበር፡፡ ከሌላው የሃገሩ ልጅ ሆፕኪንስ ጋር ሆነው በግራ መስመር ጥሩ ውህደት ሲፈጥሩ የእርሱ ሳይንሳዊ እግርኳስ ይበልጡን ተወዳጅ ሆነለት፡፡ ሁለቱም ተጣማሪዎች ኋላ ላይ ወደ <ሳኦ ቤንቶ> አመሩ፤ እዚያ በፍጥነትና ተቀያያሪ በሆነ መንገድ የሚያደርጓቸው አጫጭር ቅብብሎች <ታብሊንሃ> የሚል መጠሪያ ወጣላቸው፡፡ የቃሉ ግርድፍ ትርጉም “ትንሽ ንድፍ” የሚል ፍቺ ይሰጣል፡፡

አይዳን ሃሚልተን <አን ኢንታየርሊ ዲፈረንት ጌም> በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንዳብራራው በዩሯጓይ ወይም በአርጀንቲና ካረፈውም በላይ የብሪታኒያ ተጽዕኖ በብራዚል ይበረታ ነበር፡፡ በሪዮ ዲ ጂኒዬሮ የመምህርነት ሙያ ላይ ለመሰማራት የቀረበለትን ግብዣ ከመቀበሉ በፊት በሊቨርፑል የመሃል አጥቂ ሆኖ ስለተጫወተው ሃሪ ዌልፌር ጋዜጠኛው ማዛኒ ሲናገር ” ዌልፌር ፍሎሚኔንሴን ከተቀላቀለ በኋላ የራሱን ሐሳቦች እያሰረጸም ቢሆን ከአጨዋወት ዘይቤያችን ጋር ተላመደ፡፡” ብሏል፡፡ ማክስ ቫለንቲም ደግሞ <ኦን ፉትቦል ኤንድ ኢትስ ቴክኒክ> ላይ እንዳሰፈረው በክለቡ የነበሩና ከመሃል አጥቂው (Center-Forward) ግራና ቀኝ የሚጫወቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን ዝግ አደረጃጀት በቀላሉ የሚያስከፍቱ ሰንጣቂ ቅብብሎችን (Through-Balls) እንዴት መከወን እንዳለባቸው ያስተማራቸው ዌልፌር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ አሰልጣኙ ሌሎች ሁለት መሰረታዊ የድሪብሊንግ አደራረግ ዘዴዎችንም አሳይቷቸዋል፡፡ ” አንደኛው እንግሊዞች Swerving /በድንገት ወደ ሌላ አቅጣጫ የመዞር እንቅስቃሴ/ በማለት የሚጠሩት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች የሚታለሉባቸው ቴክኒካዊ ዘዴዎችን (Break-and-Feints) የሚያካትተው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኳስን እግር ሥር አድርገው እየሮጡ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ሸርተቴ ሲወርድ በመዝለል የሚታለፍበትን ስልት ነው፡፡” ይላል ጽሁፉ፡፡

በብራዚል እግርኳስ የሃገሬው ተወላጆች  (Locals) ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ሲጀምሩ ከጥንቱ የአጨዋወት መንገድ የመውጣት አዝማሚያ ይታይ ጀመር፡፡ ፍሎሚኔንሴ የሃገሪቱን ዜጎች ወደ ክለቡ እንዳይገቡ በመከልከሉ ተመልካቾች ከሜዳው አጎራባች መኖሪያ ቤቶች ጣራ ላይ ተንጠልጥለው ጨዋታውን ሲመለከቱ ከክሪኬት አንጻር ለመረዳት በጣም ቀላል፣ ለመተግበርም የማያዳግት ሆኖ አገኙት፡፡ ጎዳናዎች ላይ ባሉ መደበኛ ያልሆኑ መጫወቻ ስፍራዎች ከቁርጥራጭ እራፊ ጨርቆች የተሰራ ቅሪላ እየገፉ በሚጫወቱ ወጣቶች አማካኝነት ከነባሩ እግርኳስ ሙሉ በሙሉ የተለየ የጨዋታ አረዳድ ተፈጠረ፡፡ ቀጥተኛ ያልሆነውና የተጫዋቾች ግላዊ ክህሎት ላይ የሚመረኮዘው አቀራረብ ተቀባይነቱ ጨመረ፡፡ ይሁን እንጂ የተመልካቾችን ትኩረት ለመሳብ የሚያስችሉ፣ በግዴለሽነት የተጋጣሚ ተጫዋቾች ላይ የሚደረጉ ክብረ-ነክ ቴክኒካዊ ማታለያ እንቅስቃሴዎች በየትኛውም የህግ ማዕቀፍ እገዳ የሚደረግባቸውና በማኅበረሰቡም የሚወገዙ አለመሆናቸው ማክሊንን አላስደሰተውም፡፡ በሳኦፖሎ ስለነበረው የእግርኳስ ድባብ ሲናገርም ” እዚያ በጣም ታላላቅ ተጫዋቾች ነበሩ፤ ነገር ግን ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ችግር ተጸናውቷቸዋል፤ በስኮትላንድ ቢሆን ኖሮ ይህ ሥርዓት አልባ የቧልት እንቅስቃሴያቸው ፍጹም በቸልታ አይታለፍም፡፡” ይላል፡፡

በብራዚል እግርኳስና <ሳምባ> ተብሎ በሚጠራው ባህላዊ ጭፈራ መካከል አያሌ ተመሳስሎዎች (Parallels) ተፈጥረዋል፡፡ በ1958ቱ የዓለም ዋንጫ ብራዚላውያን ደጋፊዎች ሃገሪቱ የመጀመሪያዋን ዋንጫ አሸንፋ በታላቁ ውድድር ቁንጮ ሆና ሲያገኟት ድሉን ያከበሩት “ሳምባ-ሳምባ” በተሰኘ መዝሙር ነበር፡፡ ታዋቂው የእግርኳስ ጸሃፊ ሳይመን ኩፐርም <ፉትቦል አጌይንስት ዘ-ኢኔሚ> የተባለ መጽሃፍ ላይ ፔሌን ከ<ካፖዔሪስታ> ጋር ሲያነጻጽር ይስተዋላል፡፡ ካፖዔሪስታ በቅኝ ግዛት ዘመን በአንጎላውያን ቅኝ ተገዢዎች የተፈጠረና ያለ ጦር መሳሪያ ራስን ከጥቃት የመከላከል ስልት ላይ የሚያተኩር የስፖርት አይነት (Martial Art) ሲሆን ባሮቹ በገዢዎቻቸው ከሚደርስባቸው አካላዊ ጥቃት ወይም ግርፊያ ለማምለጥ በዳንስ እንቅስቃሴ እንደሚያሞኟቸው የሚያሳይ ውዝዋዜ ነበር፡፡

በወቅቱ እግርኳስን ከፈጠራ ጋር የሚያስተሳስሩ በርካታ መላምቶች ቀርበዋል፤ የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው ሮበርት ዳማታም <ጄይቲንሆ> የተባለ ኅልዮት ይዞ ከተፍ ብሏል፡፡ በቀጥታ <ትንሿ መንገድ> በሚል ሊተረጎም የሚችለው ይህ መላምት ብራዚላውያን ራሳቸው በፈጠራ ችሎታቸው እጅግ እንደሚኮሩ ያብራራል፡፡ በ1888 የባርያ አሳዳሪ ሥርዓት ተገርስሶ እንኳ የሃገሪቱ ህግጋትና ደንቦች ባለጸጎቹንና ባለ ስልጣናቱን ለመጠበቅ ተመቻችተው የተረቀቁ እንደነበሩ ያወሳል፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱ ግለሰብ በእነርሱ ዙሪያ ለመገኘት ምናባዊ መንገድ የማበጃጀት ግዴታ እንደተጋረጠበት ይጠቅሳል፡፡ ይህም በመሰረታዊ እውነታነት እየታሰበ ለበርካታ ጊዜያት ዘልቋል፡፡ <ዋት ሜክስ ብራዚል – ብራዚል!> የተሰኘው መጽሃፉ ላይ ዳማታ ስለ ጄይቲንሆ ሲጽፍ ” ጽንሰ ሐሳቡ ከፍተኛ የመመሪያዎችን ጥሰት ከመፈጸም በተጻራሪ ፥ በህግ ፣ ህግጋቱ በተገቢው መንገድ በሚተገበሩባቸው ሁኔታዎች እና በማስከበሩ ላይ ተሳትፎ በሚያደርጉ አካላት መካከል ምንም ዓይነት ነውጦች ሳይፈጠሩ የስብዕና እርቅ መፍጠሪያ ድልድይ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ህግጋቱ አስገዳጅ ይሆናሉ፤ አልያም ከነጭራሹ አይኖሩም፡፡ በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር የማይጣጣሙ እንዲሁም የዜጎችን ደህንነት የማያረጋግጡ አዳዲስ ድንጋጌዎችን የማርቀቅ ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደማይታይ በደንብ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ውጣ-ውረድ በሚበዛበት አሰራር ውስጥ ለሚፈጠር ሙስና (Bureaucratic Corruption) በር ይከፍታል፤ የህዝብ መገልገያ ተቋማት የሚጣልባቸው እምነትም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ …. አሜሪካውያን፣ ፈረንሳውያን እና ብሪታኒያውያን <ቁም!> የሚል ምልክት ሲያዩ ይቆማሉ፤ ድርጊቱ ለእኛ ብራዚላውያን ተገቢ ቢመስለን እንኳ እንደ ማኅበረሰባዊ ገራገርነት አቅልለን እናየዋለን፡፡” ይላል፡፡

እንዲያም ሆኖ ብራዚላውያን እንደነዚህ ያሉ ክልከላዎችን የሚያልፉበት መንገድ አላጡም፤ በውጪያዊ ሁኔታዎች ጥገኛ ከሚሆኑ ይልቅ በራሳቸው ላይ እምነት ጣሉ፡፡ በታሪክም ቢሆን የብራዚል እግርኳስ መለያ ባህሪ አልያም ዋነኛ መገለጫ ሃሳበ-ሰፊነታቸው (Imaginativeness) መሆኑ ከዚህ ዓይነቱ የተለየ አቋማቸው እንደመነጨ መረዳት አያዳግትም፡፡ ተጫዋቾች በተናጠል ብቃታቸው የእግርኳሱ ከባቢ ላይ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ይጥራሉ፤ በዚህም ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ እና የቡድን ሥራ ላይ የእምነት ማጣት እየሰፈነ ሄደ፡፡

አብዛኞቹ የዳማታ ሥራዎች በ1930ዎቹ መጨረሻ ብዙ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ማበርከት የጀመረውን የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪ ጂልቤርቶ ፍሬይሬን አስተሳሰብ መቅረጽ ችለዋል፡፡ ፍሬይሬ ብራዚል የበርካታ ብሄር-ብሄረሰቦች መገኛ ሃገር መሆኗን በአዎንታዊ ጎን የመቃኘት ጅምር ያሳየው የመጀመሪያው እውቅ ሶሺዮሎጂስት ለመሆን በቅቷል፡፡ በሪዮ ዲ ጂኔይሮ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ በነባሩ ነዋሪ /ካሪዮካውያኑ/ ዘንድ የተንሰራፋውን ሥራ ፈትነት አልያም በህዝቡ አጠራር የ<ማላንድሮ> ልማድን ከማጣጣል ይልቅ ለማሞጋገስ ወደኋላ የማይል፣ ቅይጥ ዘር ያለው፣ በፈጠራ ወሬ ሰዎችን የሚሸውድና አስማተኛም ጭምር ነበር፡፡ ፍሬይሬ የታደለውን አዕምሯዊ ብቃት በቲዎሪና ስልጣን የሚበልጡትን አካላት የሚልቅበት መንገድ አድርጎት ታይቷል፡፡ ” የእኛ እግርኳስ አቀራረብ ስልት ከአውሮፓውያኑ ጋር ሲተያይ የብዙ አስገራሚ ችሎታዎች ስብስብ ከመሆኑ አኳያ ሰፊ ልዩነቶች ይስተዋሉበታል፡፡ እግርኳሳችን በውስጡ የያዛቸውን እልህ፣ ብልጣብልጥነት፣ ንቃት፣ ቅልጥፍና፣ ብልህነት እና የግል ተሰጥኦ ስናይ ከአውሮፓውያኑ አንጻር ተቃርኖ ይነበብበታል፡፡ ቅብብሎቻችን፣ ልምምዶቻችን፣ ከኳሱ ጋር የምንፈጥረው ሕብር፣ የንክኪዎቻችን ውበት፣ አዝናኝ አጨዋወታችን እና የብራዚል ዘይቤ መገለጫ የሆኑት አብዶዎቻችን የእግርኳሳችን ማጣፈጫዎች ናቸው፡፡ …ቴክኒካዊ ማታለሎችን የሚያዘወትሩ ተጫዋቾቻችን ደግሞ ደማቅ የሜዳ ላይ ድባብ በመፍጠር ለሥነ-ልቦና ባለ ሙያዎች እና የህብረተሰብ ጥናት አድራጊዎች በዛሬው ዘመን የእውነተኛ ብራዚላዊ የጨዋታ ዘይቤ ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ በጣም በሚማርክ ሁኔታ የሚያሳዩ ይመስላል፡፡” ሲል በ1938 ጽፏል፡፡

የጊዜው ጸሃፍት ግዑዝ የሆኑ ነገሮችን እንደ ሰው ማየት አልያም ማናገር ስለሚመለከተው የማላንድሮ መንፈስ ለመጻፍ በ1930ዎቹ የጎመሩትን ሁለት ታላላቅ ብራዚላውያን ተጫዋቾች ማለትም የመሃል አጥቂው ሊዮኒዳስን እና ተከላካዩ ዶሚኒጎዝ ዳ ጉያን ወክለዋል፤ ሁለቱም እግርኳሰኞች ጥቁሮች ነበሩ፡፡ ዶሚኒጎዝ በግልጽ እንዳመነው የእርሱ የፈጠራ ችሎታና ኳስ ከኋላ ተቀብሎ ወደ ፊት የማሰራጨት ቴክኒካዊ ክህሎቱ በመጀመሪያ ራስን ከአደጋ በማዳን ፍላጎት የተጸነሱ ነበሩ፡፡ ” ዘወትር በአካባቢዬ ጥቁር ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በተጋጣሚ ተጫዋቾች ላይ ጥፋት ሲፈጽሙ አልያም መጠነኛ ስህተት ሲሰሩ ቅጣት ሲፈጸምባቸው ስለምመለከት በልጅነቴ ኳስ መጫወት እፈራ ነበር፡፡ ታላቅ ወንድሜ ‘ድመት ሁሌም እግሮቿ ላይ ታርፋለች፤ ውዝዋዜ ላይ ጥሩ አይደለህምን? ‘ እያለ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ጥሩ ተወዛዋዥ ስለነበርኩ እግርኳስ ስጫወት ጠቀመኝ፤ ወገቤን እንደፈለግሁ ወደ ግራ-ቀኝ አንቀሳቅስ ነበር፡፡ ያን አጭር የድሪብሊንግ ቴክኒክ የፈጠርኩት <ሙይዲንሆ> ከተባለው የሳምባ ጭፈራ አይነት ነው፡፡” ይላል፡፡

በ1919 የብራዚላውያን መሆኑ በግልጽ የሚያሳብቅ የአጨዋወት ዘይቤ መተግበር ተጀመረ፤ በዚያው ዓመት ኅዳር ወር <ስፖርትስ> የተሰኘ በሳኦፖሎ የሚታተም መጽሄት ” የብራዚሎች ግኝት” የሚል ርዕስ ያለው ጽሁፍ በመጀመሪያ ቅጹ ይዞ ወጣ፡፡ ” ‘የፊት መስመር ተሰላፊዎች ኳስን የተጋጣሚ ግብ ክልል ድረስ በመውሰድ ከቅርብ ርቀት (Closest Possible Range) ላይ የጎል ሙከራዎችን ያድርጉ!’ ከሚለው የብሪታንያውያን እግርኳሳዊ አስተምህሮ በተቃራኒው ብራዚላውያኑ ” ‘ጠንካራ ምቶች – ትክክለኛ፣ ልኬታቸውን የማይስቱና ኢላማቸውን የጠበቁ ይሁን እንጂ ከየትኛውም ርቀት ሊመቱ ይችላሉ፡፡ በአንድ የጎንዮሽ መስመር የሚቆሙ ሁሉም አጥቂዎች በጋራ እንዲንቀሳቀሱም አይገደዱም፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታና በከፍተኛ ፍጥነት የተደራጀን የባላጋራ ተከላካይ ክፍል የሚያስከፍቱ ከሆነ ሁለት ወይም ሦስት አጥቂዎች ወደፊት መግፋት በቂ ይሆናል፡፡’ ” ሲል ጽሁፉ ስለ ሁለቱ ሃገራት እግርኳሳዊ አስተሳሰብ ልዩነት ያብራራል፡፡
…የተጋጣሚ ቡድን ግብ አፋፍ ላይ ሲደርስ የስልነት ችግር ይታይበት ነበር፡፡’ በሚል የእንግሊዝ እግርኳስ ላይ ይሰነዘር የነበረው አስተያየት እንግዳ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳ የብሪታኒያ የቀጥታ ጨዋታ አስተላላፊዎች ኃይለኛ ትችት አቅራቢዎች ቢሆኑም የማዕከላዊ አውሮፓ ቡድኖች እጅጉን ክብደት እንደተሰጣቸው ያስባሉ፡፡ ምናልባት ሁሉም ነገሮች በቀላሉ በአንጻራዊነት ይታዩ ይሆናል፤ ምናልባትም ዋንደረርስን የፈጠሩት መጤዎቹ ስኮትላንዳውያን ድልድዩን አበጃጅተው ሊሆን ይችላል፥ ያ ፍርዱን የተለያየ ገጽታ ያላብሰዋል፡፡ እንዲያው ምናልባት የ<ጨዋታ ውጪ> ህግ ከመቀየሩ ስድስት ዓመታት በፊት የነበረው የብሪታንያ እግርኳስ ከዚያ በኋላ ከታየው ይበልጡን ተወሳስቦም ይሆናል፡፡ እውነታው ምንም ይሁን ምን የብራዚሎች አጨዋወት ከቡድን ስራ (Team-Work) ይልቅ የግል ፈጠራ (Self-Expression) ላይ አተኩሯል፡፡

በእነዚያ ዘመናት ከየትኛውም የብራዚል ክፍለ ሃገራት በላቀ እግርኳስ በሪቨር ፕሌት የመመንደግ ሒደት አሳይቷል፡፡ ብራዚል በዓለምአቀፍ ደረጃ ከአርጀንቲና፣ ኡሯጓይ ወይም ቺሊ ጋር ባካሄደቻቸው የመጀመሪያዎቹ አስር ጨዋታዎቿ ያሳካችው ሦስት ድልም ብቻ ነበር፡፡ በ1917ቱ የኮፓ አሜሪካ ውድድርም በአርጀንቲናና ኡሯጓይ አራት አራት ግቦች ተቆጥረውባታል፡፡ በ1919ኙ ውድድር ግን የተሻለ ሆነው ቀረቡ፤ አንደኛውን የመስመር ተከላካይ ሙሉ በሙሉ የመከላከል ሃላፊነት ብቻ እንዲወጣ አደረጉ፤ ሌላኛው ደግሞ የማጥቃት ሒደቱ ላይ በነጻነት የመሳተፍ ፍቃድ ተሰጠው፤ ምስጋና ለዚህ መፍትሄ ይግባና ብራዚል ይህኛውን የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ዋንጫ አሸነፈች፡፡ በእርግጥ ውሳኔው ያን ያህል ውስብስብ ብልሃት አልጠየቀም፤ ይሁን እንጂ የሃገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ውሳኔ ለመጀመሪያ ጊዜ የመከላከል አደረጃጀት አስፈላጊነትን እውቅና እንዲያገኝ አድርጓል፡፡

ብራዚል በላቲን ሃገራቱ ውድድር ያሳካችው ድል ዘላቂ አህጉራዊ የበላይነት እንዲኖራት አላገዛትም፡፡ ከ1940 በፊት ከአርጀንቲና ጋር ባከናወነቻቸው ሃያ ጨዋታዎች በስድስቱ ብቻ ልታሸንፍ ቻለች፤ ከኡሯጓይ ጋር ደግሞ አስራ ሦስት ግጥሚያዎችን አድርጋ አምስቱን ረታች፡፡ በ1921 በአህጉሪቱ የዋንጫ ውድድር በድጋሚ ቁንጮ መሆን ብትችልም ለሶስተኛ ጊዜ ድሉን ለመቀዳጀት እስከ 1949 ድረስ መጠበቅ ግድ ሆኖባታል፡፡ (የሚያስደንቀው ነገር ብራዚል በሌላ ሃገር የተዘጋጀ ውድድር ለማሸነፍ እንዲሁም አምስተኛ ድል ለመጎናጸፍ 1997 ድረስ መታገስም ተጠብቆባታል፡፡)

በብራዚል እግርኳስ ማኅበር ውስጥ በተፈጠረው ሽኩቻ ምክንያት በ1930ው የዓለም ዋንጫ ሃገሪቱ ከካሪዮካ ግዛት ብቻ በተመረጡ ተጫዋቾች ልትወከል ተገደደች፡፡ በውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ በዩጎዝላቪያ 2-1 ተረታች፤ በተከታዩ ግጥሚያ ቦሊቪያን 4-0 ቢትደቁስም ከኡሯጓይ በጊዜ ከመሰናበት አልዳነችም፡፡ ” ብራዚሎች በተጫዋቾች የተናጠል ብቃት ምርጥ ነበሩ፡፡ ሆኖም በቡድን ስራ ዝቅተኛ ደረጃን አሳዩ፡፡” ሲል ብሪያን ግላንቪል ጽፏል፡፡

በ1933 <ፕሮፌሽናሊዝም> በአግባቡ መከበር ጀመረ፤ ከክለቦቻቸው ጋር ለጉብኝት ወደ አውሮፓ የሚሄዱ ብራዚላውያን ተጫዋቾች ወደ ሃገራቸው የመመለስ ፍላጎት እያደረባቸው መጣ፡፡ ሆኖም የብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ላይ አልያም የአጨዋወት ዘይቤዓቸው ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደርና መሻሻል ለማሳየት ጊዜ ወሰደ፡፡

ብራዚሎች በ1934ቱ የዓለም ዋንጫም ከአንድ ጨዋታ በላይ መዝለቅ አልቻሉም፤ በስፔን 3-1 ተሸነፉና ጓዛቸውን ሸክፈው ከጣልያን ወጡ፡፡ ከዚያም ለዓለም ዋንጫው ማለፍ ካልቻለችው ዩጎዝላቪያ ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ ለማድረግ ወደ ቤልግሬድ አመሩ፡፡ እዚያም ከባድ ሽንፈት ተከናነቡ፤ ዩጎዝላቪያ 8-4 ረመረመቻቸው፡፡ ይህ ብሄራዊ ቡድን እንደ ዶሚኒጌዝ፣ ሊዮኒዳዝ እና ዋልደማር ደ ብሪቶን የመሳሰሉ ታላላቅ ተጫዋቾችን ያቀፈ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብራዚላውያኑ ከእነርሱ የማይጠበቅ ታክቲካዊ ገራገርነት ያጠቃቸው ነበር፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በሞንቴቪዲዮ ካሳዩት ደካማ አቋም በከፋ መጠን ለተጋጣሚዎቻቸው ተጋላጭ ሆነው ቀረቡ፡፡ የእግርኳስ ታሪክ ምሁሩ ኢቫን ሶተር ” የብራዚል ተጫዋቾች በመስመሮች መካከል (Between-The-Lines) ሰፋፊ ክፍተቶችን ይተዋሉ፤ ዩጎዝላቪያዎች ደግሞ እነዚያን ክፍት ቦታዎች በአግባቡ ይጠቀሙበታል፡፡ ይህም የጥንቱ አጨዋወት ሥርዓት (Old-Fashioned System) በርካታ ህጸጾች እንዳሉበትና ሊቀየር እንደሚገባው ግልጽ ማሳያ ነበር፡፡” ሲል ከቤልግሬዱ ጨዋታ በኋላ ችግሩን ለማብራራት ጥሯል፡፡


ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡