ክልል ክለቦች ሻምፒዮና፡ ጂኮ ከተማ በተጫዋች ማጭበርበር ከፍተኛ ቅጣት ተላለፈበት

በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ምድብ አምስት ቀዳሚ ሆኖ አጠናቆ የነበረው ጂኮ ከተማ የተሰኘው ቡድን የተሳሳተ መጠርያ ስም በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ ተጫዋች በማሰለፉ ከውድድር ታግዷል።

ከጋንቤላ ክልል ተወክሎ የሚጫወተው ቡድን ዋና ስሙ ኪቲካ ጅማ የተሰኘ ተጫዋችን በ2011 የውድድር ዘመን ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለኢትዮጵያ ቡና እየተጫወተ እና የአንድ ዓመት ውል እያለው “አናሪ ጅማ” በሚል ስሙን በመቀየርና የመታወቂያ ቴሴራ በማስወጣት ለጂኮ ቡድን ተሰልፎ ስለመጫወቱ ማስረጃ ተገኝቶበታል።

በመሆኑም ተጫዋቹ የተሳሳተ መጠርያ ስም ተሰጥቶትና የክለብ ተጫዋች መሆኑ እየታወቀ በተጭበረበረ መታወቂያ ተሰልፎ በመጫወቱ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል

* በሀሰተኛ ስም አናሪ ጅማ በመባል ትክክለኛ ስሙ ኪቲካ ጅማ መባሉ እየታወቀ የሀሰት መታወቂያ አውጥቶ በመጫወቱ ለአንድ ዓመት ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ ታግዷል።

* የጂኮ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ማኑቹ ዶስ በተጭበረበረ ስም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ፍለጋ ህግ ጥስ በመገኘታቸው ለአንድ ዓመት ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ ታግዷል።

*የጂኮ ቡድን መሪ አቶ ቾል ሮት በተጭበረበረ ስም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ፍለጋ ህግ ጥስ በመገኘታቸው ለአንድ ዓመት ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ ታግዷል።

*የጂኮ ቡድን ቀደም ሲል ባደረጋቸው ውድድሮች ላይ ተገቢ ያልሆነ ተጫዋች በማሰለፍ ያገኙዋቸው ውጤቶች በሙሉ ተሰርዘው ለተጋጣሚ ቡድኖች 3-0 የሆነ ውጤት በመስጠት 3 ነጥብና 3 ተደማሪ ግብ እንዲመዘገብላቸው ተወስኗል።

በክልል ክለቦች ሻምፒዮና በተሳሳተ መታወቂያ ተጫዋቾችን ማሰለፍ አዲስ ክስተት አይደለም። ከሁለት ዓመት በፊትም በተመሳሳይ አረካ ከተማ ሰባት ተጫዋቾችን በተሳሳተ መታወቂያ በማጫወት ከውድድሩ መታገዱ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና በምድብ ሀ ሰመራ ሎጊያ ውድድሩን ማቋረጡ የሚታወስ ሲሆን ከሁለት ጨዋታ ተጫውቶ አቋርጦ የወጣ በመሆኑ በቀሪው ሁለት ጨዋታ ፎርፌ እንዲሰጥ ተወስኗል። በተመሳሳይ በምድብ 5 አቋርጦ የወጣው አሳይታ ከተማ ደግሞ አንድ ጨዋታ ብቻ የተጫወተ በመሆኑ የተመዘገበው ውጤት ተሰርዞ በሦስት ቡድኖች ውድድሩ እንዲቀጥል ተወስኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡