ናሚቢያዊው አጥቂ ወልዋሎን ለመቀላቀል ተቃርቧል

ወልዋሎ ዓ/ዩ የመጀመርያ ፈራሚውን በእጁ ለማስገባት ተቃርቧል።

ባለፈው ዓመት መጀመርያ ቱራ ማጂክን ለቆ ድሬዳዋ ከተማን በመቀላቀል ከቡድኑ ጋር መልካም ዓመት ያሳለፈው ናሚቢያዊ አጥቂ ኢታሙና ኬይሙኒ የቀድሞ አሰልጣኙን ፈለግ ተከትሎ ወልዋሎ ለመቀላቀል ተቃርቧል። በአፍሪካ ዋንጫው ከናሚቢያ ጋር ተሳታፊ የነበረው ይህ የ26 ዓመት አጥቂ ባለፉት ሳምንታት በሀገሩ ሚዲያዎች ስሙ ከደቡብ አፍሪካ ክለቦች ጋር እየተያያዘ ቢቆይም በስተመጨረሻ እንደቀድሞው አሰልጣኙ ሁሉ ፊቱን ወደ ቢጫ ለባሾቹ አዙሯል።

ከዋና አሰልጣኛቸው ዮሐንስ ሳህሌ ጋር ለመቀጠል የተስማሙት ቢጫ ለባሾቹ የለቀቁባቸውን ሦስት ተጫዋቾች ቦታ በዝውውር ይሞላሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነባር ተጫዋቾች ውል የማራዘም ስራንም የሚያከናዉኑ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ከዛሬ ጀምሮ በሰፊው ወደ ዝውውሩ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ክለቡ ከኢታሙና በመቀጠል ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን ለማምጣትም እንቅስቃሴ መጀመሩን ማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡