በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ አንደኛ ሊግ ያደጉ ቡድኖች ታውቀዋል

ከሐምሌ 14 ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ዛሬ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ተካሂደው ወደ አንደኛ ሊግ እግረመንገዳቸውንም ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፉ ቡድኖችን ለይቷል።

03:00 በአበበ ቢቂለ ስታዲየም ሐውዜን ከተማ እና ኮረም ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በሐውዜን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጥረት የተሞላበት ጨዋታ ሆኖ በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ጎል በማስቆጠሩ ቀዳሚ የነበሩት ኮረሞች ነበሩ። በ6ኛው ደቂቃ ሐብቱ ጊደና በጥሩ መንገድ የተቀበለው ኳስ በጥሩ አጨራረር ብቃት ባስቆጠረው ጎል ነበር ቀዳሚ መሆን የቻሉት። ኮረሞች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበት የጎል ዕድሎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙ መቅረታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ሐውዜኖች በተገኙት አጋጣሚዎች ወደ ጎል የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶላቸው 41ኛው ደቂቃ አለማት ተስፋዬ ባስቆጠረው ጎል አንድ አቻ ሆነዋል።

ከእረፍት መልስ ጉሽሚያ የበዛበት ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ ትርጉም ያለው የተሳካ የጎል ሙከራ ሳናይ እየተቆራረጠ ቀጥሎ በአንድ አጋጣሚ ሐውዜኖች ጎል አስቆጥረው ረዳት ዳኛው እንቅስቃሴ ቢያሳይም ዋናው ዳኛ ኳሱ መስመሩን አላለፈም በማለት ከሻሩት በቀር ሌላ ነገር መመልከት አልቻልንም። በመጨረሻም 80ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ሐውዜኖች ያሻገሩትን ኳስ ሀዱሽ ሰለሞን በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል ሐውዜኖች 2-1 እንዲመሩ አድርጓቸዋል።። ከዚህ ጎል መቆጠር በኃላ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ጉሽምያ የበዛበት ሆኖ ቢቀጥልም ጨዋታው በሐውዜን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሐውዜን በቀጣይ ዓመት አንደኛ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አንድ የሐውዜን ተጫዋች በኮረም ተጫዋች በደረሰበት ድብደባ ጉዳት በማስተናገዱ ለተሻለ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል።

05:00 በተካሄደው ሌላኛው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታ መከላከያ ከ ሲልቫ ከፍተኛ ፉክክር አድርገው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2-2 በማጠናቀቃቸው ወደ መለያ ምቶች አምርተው መከላከያ 4-2 ማሸነፍ ችሏል። ጥሩ እግርኳስ ከጥሩ ዳኝነት ጋር በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰደው ሲልቫ ነበር። በመከላከያ የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት በ12ኛው ደቂቃ ግርማ ነጋሽ ወደ ጎልነት በመቀየር ሲልቫዎችን ቀዳሚ አድርጓል። ጎል ቢስተናገድባቸውም አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዩት መከላከያዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደፊት በመሄድ ያገኙት የመልስምት ከተከላካዮች መሐል ተደርቦ ሲመለስ ደረጄ ግዛው አግኝቶ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል። ከደቂቃዎች በኃላ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች የቡድኑን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እና ለአጥቂዎች ነፃ ኳስ በመስጠት አቅም እንዳለው እያሳየ የሚገኘው አማካይ መሳይ ቢተውልኝ ከርቀት ባስቆጠረው ግሩም ሁለተኛ ጎል መከላከያዎች መምራት ችለዋል። አከታትለው መከላከያዎች ጎል ማስቆጠራቸው ሲልቫዎች ቢደናገጡም የኃላ የኃላ ተረጋግተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።

ከእረፍት መልስ ሲልቫ የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ይዘገይ እንጂ ከመከላከያ በተሻለ ተጭኖ ተጫውቷል። ሲልቫ የአቻነት ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ ፊት ሲሄዱ መከላከያ ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኃላ አፈግፍጎ መከላከሉ ላይ አመዝኖ ተጫውቷል። በመጨረሻም የጨዋታው መጠናቀቂያ 89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ታዲዮስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያቀበለውን ኳስ ሱራፌል ዓለማየሁ ወደ ጎልነት ቀይሮ ሲልቫዎችን ሁለት አቻ አድርጓል። በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት እና ፌደራል ዳኛ አህመድ ሲራጅ በጥሩ ሁኔታ ተመርቶ የተጠናቀቀው ይህ ጨዋታ ወደ መለያ ምት አምርቶ መከላከያዎች በግብ ጠባቂያቸው ብቃት ታግዘው 6-5 በማሸነፍ ወደ አንደኛ ሊግ ማደጋቸውን አረጋግጠዋል።

07:00 በቀጠለው ሁለቱን የደቡብ ክልል ቡድኖች ያገናኘው የሾኔ ከተማ እና የቦዲቲ ጨዋታ በሾኔ ከተማ የበላይነት 4-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በተደራራቢ ጨዋታዎች ተዳክመው የቀረቡት ቦዲቲዎች ደካማ እንቅስቃሴ ባሳዩበት ጨዋታ ልምድ ባላቸው ተጨዋቾች የተገነባው ሸኔ በተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል። የ24ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎል ደገፍ አድርጎ በመምታት ወንድማገኝ ኢዮብ ለሾኔ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል። እልህ በበዛበት የኃይል እንቅስቃሴ ጨዋታው እየተቆራረጠ ቀጥሎ 36ኛው ደቂቃ ቦዲቲዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ግርማ መስፍን ጎል አስቆጥረው አንድ አቻ መሆን ችለዋል።

ከእረፍት መልስ ልምዳቸውን ተጠቅመው ተረጋግተው የሚጫወቱት ሾኔዎች የቦዲቲ ተጫዋቾች ጎል ፍለጋ የሜዳ ክፍላቸውን ለቀው ለማጥቃት በሄዱበት አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ወንድማገኝ ኢዮብ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ረጃጅም ኳስ በመጫወታቸው የተዳከሙት ቦዲቲዎች ላይ ብልጫ ለመውሰድ የረዳቸው ሾኔዎች 81ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው እስራኤል ሙላቱ አማካኝነት ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ይህች ጎል ስትቆጠር ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ የሾኔ ተጫዋቾች ደስታቸውን ሲገልፁ ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ አምበሉ ዳግም ወርቁ በተቀመጠበት የዕለቱ ዳኛ በቀይ ካር ከሜዳ አስወግደውታል። በመጨረሻም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በሾኔ በኩል ጥሩ ይንቀሳቀስ የነበረው ደረጄ ጥላሁን የግብ ጠባቂውን ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክቶ በአየር ላይ አሾልኮ አራተኛ ጎል አስቆጥሯል። በተመሳሳይ ጎል ሲቆጠርባቸው የተበሳጨው የቦዲቲው ተጫዋች አማኑኤል ሰለሞን ሆን ብሎ የሾኔ ተጫዋችን በኳስ በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ሾኔ ከተማም ጨዋታውን 4-1 አሸንፎ ሌላኛው ወደ አንደኛ ሊግ ያደገ ቡድን ሆኗል።

09:00 የዕለቱ የአበበ ቢቂላ የመጨረሻ የሆነው የአቃቂ ማዞርያ እና የደጋን ከተማ ጨዋታ በደጋን ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩት ደጋኖች በጥሩ የኳስ ቅብብል ሳጥን ውስጥ በመግባት በ15ኛው ደቂቃ በያሬድ ሽመልስ አማካኝነት የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። ፍፁም ተዳክመው ሜዳ ላይ ያልነበሩት አቃቂ ማዞርያዎች በመጀመርያው አጋማሽ ምንም አይነት ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር። ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ደጋኖች በጀማል መሐመድ አማካኝነት ሁለተኛ ጎላቸውን አስቆጥረዋል።

ከእረፍት መልስ ወድያውኑ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን አጋጣሚ መፍጠር የቻሉት አቃቂ ማዞርያዎች ተቀይሮ በገባው ብዙነህ በየነ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው የጎል ልዩነቱን አጥብበዋል። የጨዋታው ፉክክር ጨምሮ አቃቂ ማዞርያዎች በሁለት አጋጣሚዎች የጎል አጋጣሚዎች ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። 79ኛው ደቂቃ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ያሬድ ሽመልስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል ለደጋን ከተማ አስቆጥሯል። በመጨረሻም 89ኛው ደቂቃ አቃቂ ማዞርያዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ግርማ ዳቢ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የጎል ልዩነቱን ቢያጠብም በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በደጋን 3-2 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ደጋኖች ወደ አንደኛ ሊግ ማደጋቸውን አረጋግጠዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የአቃቂ ማዞርያ ተጫዋቾች የዕለቱን የመሐል ደኛ በመደብደብ ያሳዩት ያልተገባ ባህሪ መታረም የሚገባው ድርጊት ነው።

በሌላ ሜዳ በተካሄዱ ጨዋታዎች የተመዘገቡ ውጤቶች

መኩይ 0-3 ኤጀሬ ከተማ*

*ሀሳሳ ከተማ
3–0 አኳድሬ
ምዕራብ ዐባያ 1–1 ፈራውን ከተማ*
(በመለያ ምት ፈራውን 6–5 አሸንፏል)

*ኣብዲ ሱሉልታ
2–1 ሞጣ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡