የነገው የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ጨዋታ ክርክር አስነስቷል

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ አስመልክቶ አመሻሽ ላይ በተካሄደው ቅድመ ስብሰባ ላይ ዩጋንዳዊው ኮሚሽነር ጨዋታው በዝግ መካሄድ አለበት በማለት መናገራቸው ክርክር አስነስቷል።

ነገ 10:00 ከሚካሄደው የመልስ ጨዋታ አስቀድሞ ዛሬ አመሻሽ 02:00 በኤሜ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው ቅድመ ስብሰባ የጨዋታው ኮሚሽነር የሆነት ዩጋንዳዊው ማይክ ቼን ባ ከጨዋታው አስቀድመው የሜዳውን አጠቃላይ ገፅታ የጎበኙ ሲሆን በቅድመ ስብሰባው ወቅት የድሬዳዋ ስታዲየም ማሻሻያ ስራዎች እየተደረጉበት በመሆኑ “አሁን ካለበት ሁኔታ አንፃር የፀጥታ ችግር ቢፈጠር ሜዳው አጥር የሌለው በመሆኑ ኃላፊነት መውሰድ አስቸጋሪ ነው። በዚህ ሜዳ ላይ ውድድር ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ ጨዋታው በዝግ መካሄድ አለበት።” በማለት ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኃላ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወከሉት አካላት “የፀጥታ ችግር የሚያስፈጥር ምንም ዓይነት ችግር የለም። በቂ የፀጥታ ኃይል አለን። ድሬዳዋ እና ጅቡቲ ሁለት የተለያዩ ሀገሮች ቢሆኑም አንድ ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው አንድ ህዝብ ናቸው። ስለዚህ ምንም የተለየ የሚያሰጋ የፀጥታ ችግር የሌለ በመሆኑ ጨዋታው ለተመልካች ክፍት መሆን አለበት።” በማለት ተናግረዋል።

የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን በበኩላቸው “ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ምንም የሚያሰጋን የፀጥታ ችግር ያልተመለከትን በመሆኑ ጨዋታው ለተመልካች ክፍት ሆኖ ቢካሄድ ችግር የለውም በማለታቸው ዩጋንዳዊው ኮሚሽነር በስታዲዮሙ የሚገኙ አንዳንድ ቁሳቁሶች ከሜዳው እንዲነሱ በማዘዝ ጨዋታው በክፍት ሜዳ እንዲካሄድ ተስማምተው ወጥተዋል።

በተያያዘ ዜና ነገ 10:00 በሚካሄደው ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ጨዋታ የስታዲየም ተመልካች መግቢያ ይፋ ሆኗል።

ክቡር ትሪቩን – 100 ብር
ኮተን ትሪፕ (ቀኝ ጥላ ፎቅ) 50 ብር
ባቡር ትሪፕ (ግራ ጥላ ፎቅ) 50 ብር
ከማን አንሼ – 30 ብር
ካታንጋ – 10 ብር


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡