ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ተጫዋቾቹን አስፈረመ

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባለፉት ዓመታት በደደቢት ጥሩ ጊዜ ያሳለፉት ሁለት አማካዮች ያብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለን አስፈርመዋል።

ፈረሰኞቹ ለቀጣይ የውድድር ዓመት በአማካይ ክፍል ላይ ያላቸው የተጫዋቾች ይዞታ በተወሰነ መልኩ ይለውጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ የያብስራ ተስፋዬ ዝውውር የዚህ አካል ነው። ከደደቢት ሁለተኛ ቡድን አድጎ ቡድኑን በአምበልነት እስከ መምራት የደረሰው ተስፈኛው አማካይ ያብስራ ባለፈው ዓመት በጉዳት ምክንያት ዘግይቶ ከቡድኑ ጋር ቢቀላቀልም መጥፎ የውድድር ዓመት ባሳለፈው ደደቢት በግሉ ጥሩ ዓመት ነበር ያሳለፈው።

ሌላው ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው አማካዩ አቤል እንዳለ ሲሆን እሱም በተመሳሳይ ከደደቢት ሁለተኛ ቡድን የተገኘ ተጫዋች ነው። ባለፈው ዓመት በአመዛኙ የአሰልጣኞቹ ተቀዳሚ ምርጫ የነበረው ፈጣሪው አማካይ ጉዳት አጋጥሞት ካመለጡት ጥቂት ጨዋታዎች በስተቀር ነው ሰማያዊዎቹን በቋሚነት አገልግሏል። በውድድር ዓመቱ አምስት ለግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለው ተጫዋቹ ባለፈው ዓመት በፈረሰኞቹ ቤት የነበረበውን የተገደበ የፈጠራ አቅም በተወሰነ መልኩ ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡