“ሚድያ ሰብስቦ ሰነድ በመፈራረም የሚቀየር አንዳች ነገር የለም” – አቶ ኢሳይያስ ጂራ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጫዋቾች የደሞዝ ጣራን ለመወሰን በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ ሊሳቅ ሪዞርት የተጠራው የውይይት መድረክ ላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ አስተያየት የሰጡት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ስለወቅታዊ የሊጉ ፎርማት ለውጥ ጉዳይ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

“እያንዳንዱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አባላት በግልፅ የተቀመጠ መብትና ግዴታ አለባቸው፤ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ ላረጋግጥላችሁ የምወደው ከ144 አባላቶቻችን ውስጥ ይፋዊ በሆነ መልኩ የቀረበልን ምንም አይነት ጥያቄ የለም፡፡ ማንም አጀንዳ ያለውና በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር ይኖርብናል ብሎ የሚያስብ ባለድርሻ አካል አጀንዳ የማስያዝ መብት አለው፤ ለዚህም አጀንዳ አስይዘን መነጋገር ይኖርብናል እንጂ እዛና እዚህ ሆኖ መረባበሽ አይኖርብንም፡፡

“በይፋ ጥያቄ ባልቀረበበት ሁኔታ ማንም በገዛ ፈቃዱ ተነስቶ ሚድያ ሰብስቦ ሰነድ ስለተፈራረመ የሚቀየር አንዳችም ነገር የለም፡፡ የምንተዳደርበትና የሚገዛን ደንብ አለ፤ አጀንዳ ተይዞ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ሳይሰጥበት የሚቀየር ጉዳይ የለም፡፡”

“በእኛ በኩል በ2012 የውድድር ዘመን ሊጉ የራሱን በቻለ የሊግ ኩባንያ እንዲመራ ሰነድ አዘጋጅተን ጨርሰናል፤ ስለዚህ የጉባዔው ወቅት ሲቃረብ አጀንዳ አለኝ የሚል አካል ካለ አጀንዳውን ተቀብለን ለመወያየት ዝግጁ ነን፡፡ እዚህም እዚያም በሚነፍስ ንፋስ መረበሽ የለብንም፤ በይፋ ባልቀረበ አጀንዳ ላይ ብዙ መጨነቅ አይገባም፡፡”

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ሀሳብ ያከሉት አቶ ርስቱ ይርዳውም ተከታዮችን ሀሳቦች ሰጥተዋል፡፡

“ሁሉም የእግርኳሱ ባለድርሻ አካላት እግርኳሳችን ወደፊት በሚያራምድና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አጢነው ከስሜት ወጥተን በሰከነ መልኩ መወያየት ይኖርብናል፡፡

“ቀጣዩ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት በቅርቡ ተመሳሳይ መድረክ ጠርተን ተመካክረን የተሻለ የምንለውን አማራጭ ተግባብተን መወሰን ይኖርብናል። የተሻለ ሀሳብ ከመጣና እግርኳሱን የሚጠቅም ከሆነ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ ለመምራት ዝግጁ ነን፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡