ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ሰባት – ክፍል ሦስት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም 27ኛ ሳምንት መሰናዶ ስለ ብራዚል በሚያወሳው ምዕራፍ ሰባት ሦስተኛ ክፍል የዲያጎናል ፎርሜሽንን ውልደት እንመለከታለን። 


ከዶሪ ኩርስችነር ስንብት በኋላ ፍላቪዮ ኮስታ ወደ ፍላሚንጎ የአሰልጣኝነት መንበር ሲመለስ በሁሉም ዘንድ እንደታሰበው በድጋሚ 2-3-5 (Pyramid) ፎርሜሽንን ለመጠቀም አልወደደም፡፡ ይልቁንም <W-M> የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን- የራሱ የፈጠራ ቅርጽ በሆነው፣ <Diagonal> ሲል በሰየመውና በሠያፍ ጎነ አራት ሒሳባዊ ምስል በሚወከለው እንቅስቃሴያዊ መዋቅር ለማስተካከል ወይም ለማሻሻል ፈለገ፡፡ በመሰረቱ ፍላቪዮ ኮስታ ያደረገው በ<W-M> (3-2-2-3) ፎርሜሽን የመሃለኛው ክፍል ላይ የሚሰለፉትን አራት ተጫዋቾች በሁሉም አቅጣጫ በተመሳሳይ ርቀት የሚያገናኘውን ሒሳባዊ እኩል የጎነ አራት ምስል (ካሬ/Square) ማዕዘናዊ ጫፎቹን በትንሹ በመለጠጥ እና በመጠኑ በመግፋት ተቃራኒ ጎኖቹ ትይዩ ወደሆኑ አራት ማዕዘናት ያለው ቅርጽ ፓራሌሎግራም (Parallelogram) እንዲቀየር ማስቻል ነበር፡፡ የብራዚላዊው አሰልጣኝ አዲሱ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ መዋቅር በዋነኝነት ሶስት ተከላካዮችን ያካትታል፡፡

በኩርስችነር ዘመን ከፋውስቶ ጋር ለተፈጠረው ጠብ መንስዔ የሆነው የተከላካይ ክፍል አደረጃጀትም (Defensive Structure) ይኸው ሲስተም ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፎርሜሽኑ የማጥቃት ወረዳ ሶስት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Forwards) መገኘት ነበረባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ብሪታኒያውያኑ የተለመደ ሥልት በሜዳው ቁመት እኩሌታ ለየመስመሮቻቸው ተጠግተው የሚጫወቱት ሁለት አማካዮችን (Half-Backs) እና ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚጫወቱ ሁለት የፊት መስመር ተሰላፊዎችን (Inside-Forwards) እንዲሁ በጥንቱ ሞዴል ከማሰለፍ ይልቅ በፍላቪዮ ኮስታ <ዲያጎናል/Diagonal/ ፎርሜሽን> በጥልቁ ወደኋላ ያፈገፈገ የመስመር አማካይ (Deep-Lying Half-Back) ማጫወት አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡

የኮስታ ቀዳሚ የአሰላለፉ ግንዛቤ (Initial Conception) ተግባራዊ እየተደረገ በ1941 በተጠናቀቀው ንድፍ መሰረት በሜዳው ቁመት ለቀኙ መስመር ተጠግቶ በመሃል አማካይነት የሚሰለፈው ተጫዋች (Right-Half) ቮላንቴ ሲሆን (በአሁኑ ዘመን <Volante> የተሰኘው ስያሜ በብራዚል እግርኳስ ውስጥ የተከላካይ አማካይ /Defensive Midfielder/ ሚናን ለመጥቀስ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡) በስተግራው ደግሞ ወደፊት ተስቦ የማጥቃት ሒደቱን የሚመራው የግራ መስመር አማካዩ (Left-Half) ጃይም ሆነ፡፡ ወደኋላ ካፈገፈጉት ሁለቱ የመሃል-ፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) መካከል በቀኝ በኩል ዚዚንሆ ከጀርባው ሰፊ ክፍተት እንዳይፈጥር ታስቦ በጥቂቱ ወደኋላ እንዲመለስ ሲደረግ በስተግራ ደግሞ ፔራሲዮ ከአጣማሪው ዚዚንሆ አንጻር ለአጥቂዎቹ በቀረበ ቦታ ላይ አይነተኛውን የአጥቂ አማካይነት (Classic Attacking Midfielder/<ፖንታ ደ ላንሳ/ Ponta da lanca>)  ኃላፊነት ይወጣ ጀመር፡፡

<ዲያጎናል> ፎርሜሽኑ ሲያስፈልግ የማጥቃት ሒደቱ ወደቀኙ መስመር እንዲያጋድል በቀላሉ የእንቅስቃሴ ውቅር ለውጥ ማድረግ እንዲያስችል የሚፈቅድ ይዘት ነበረው፡፡ የ1930ው ዓለም ዋንጫ አሸናፊ የኡሯጓይ ቡድን አባል የነበረው ኡንዲኖ ቪዬራ በ<ፍሎሚኔንሴ> ይህን ፎርሜሽን ለመተግበር ሞክሯል፤ ይሁን እንጂ አሰልጣኙ ስፒኔሊን በግራ መሃል-አማካይነት (Left-Half) የመከላከል ክፍሉን እንዲመራ እንዲሁም ሮሜውን ደግሞ በሜዳው ቁመት የቀኙ-ክፍል ወደ መሃል ተጠግቶ የማጥቃት አማካይነት (Ponta da lanca) ሚና እንዲጫወት በማድረግ አጠቃላይ የፎርሜሽኑን የማጥቃት አቅጣጫ (Attacking Direction) ለመቀየር ቻለ፡፡

“<ዲያጎናል ፎርሜሽን> ምን ያህል አዲስ ነው?” የሚለው ጥያቄ በራሱ አከራካሪ ጉዳይ ነበር፡፡ የቀድሞው የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና ደራሲው ካንዲዶ ደ ኦሊቬይራ <ዘ-‘WM’ ሲስተም> በተሰኘው መጽሃፉ እንዳሰፈረው ከሆነ ፍላቪዮ ኮስታ በ<ቫስኮ ደጋማ> ክለብ ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ወደ አውሮፓ ተጉዞ “የራሴ ፈጠራ” ስለሚለው ፎርሜሽን እንዲያብራራ ሲደረግ የእርሱ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ከዋነኛው <WM> ፎርሜሽን የተወሰደና ዝቅተኛ ግምት የሚቸረው ቀጥተኛ ቅጂ መሆኑ ተደርሶበት በከፍተኛ ሁኔታ ተፊዞበታል፡፡ እውነታው ምናልባት ፍላቪዮ ኮስታ በ<WM> ፎርሜሽን በተፈጥሮ የሚገኙና እምብዛም የማይነገሩ የእንቅስቃሴ ሒደቶችን ግልጽ ማድረጉ ይሆናል፡፡ ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ ከሚጫወቱት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) መካከል አንደኛው ከሌላኛው በተሻለ ጥሩ የፈጠራ ክህሎትን ሊታደል ይችላል፤ ከመሃል አማካዮቹ (Half-Backs) መሃከልም እንዲሁ አንደኛው ይበልጡን መከላከል ላይ ያተኩር ይሆናል፡፡

<ሶከር ታክቲክስ> ላይ ቤርናርድ ጆይ በ1930ዎቹ በአርሰናል የግራ መስመር-የመሃል አማካዩ (Left-Half) ዊልፍ ኮፒንግ በጥልቀት ወደኋላ ተስቦ ሲጫወት የቀኝ መስመር-የመሃል አማካዩ (Right-Half) ጃክ ክራይስተን የቦታ ነጻነት ያገኝ እንደነበር ትንታኔውን ያቀርባል፡፡ በ1940ዎቹ መባቻና 1950ዎቹ ጅምር ዓመታት የዎልቭስ ክለብ እና የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አምበል የነበረው ቢሊ ራይት ተለምዷዊ ሚናው በመሃል-የመስመር አማካይነት (Half-Back) ቢሆንም እንደ መሃል-ተከላካይ አማካይም (Centre-Half) መጫወት ይችል ነበር፡፡ ራይት ከቢሊ ክሩክ አልያም ከጂሚ ዲኪንሰን ወደኋላ ባፈገፈገ ቦታ አልተጫወተምን? በእርግጥ መነሻ ሐሳቡ በተፈጥሮ “ግራኝ” መሆንን ከፈጠራ ክህሎት ጋር ለሚያያይዘው ጽንሰ-ሐሳብ የቅቡልነት ድጋፍ ከመስጠት አኳያም ታይቶ ሊሆን ይችላል፡፡ <ዘ-ፐርፌክት 10> ላይ ሪቻርድ ዊሊያምስ ከሜዳው ወገብ በላይ በግራ መስመር የሚሰለፍ አማካይ ተጫዋች (lnside-Left) በተቃራኒው በኩል ከሚጫወተው አማካይ (Inside-Right) ይልቅ የማጥቃት ጨዋታ ላይ መሳተፉ የተለመደ እንደነበር ያስረዳል፡፡ 8-ቁጥር መለያ ከሚለብስ የመስመር አማካይ ይልቅ 10-ቁጥር መለያ የሚለብሰው ተጫዋች እንደ ጨዋታ አቀጣጣይ ወይም የአጥቂ አማካይ (Playmaker) ተደርጎ የመታየቱ ምስጢርም ከዚህ ቲዎሪ የመነጨ አስተሳሰብ ይመስላል፡፡

ፍላቪዮ ኮስታ ላይ ጥርጣሬ ማሳደር ተገቢ ይመስላል፤ ለምሳሌ የ<ፓውሊስታ> የጨዋታዎች-ቀጥታ ስርጭት አቅራቢው አልቤርቶ ሔለና ጁኒየር ብራዚላዊው አሰልጣኝ የክሩስችነርን ሃሳቦች በድጋሚ ከመከለስ ባለፈ በራሱ የፈጠረው ነገር እንዳልነበር ለማሳወቅ ይጥራል፡፡ ጋዜጠኛው ቀደም ሲል አሰልጣኙ የኩርስችነርን እሳቤዎች ስላንኳሰሰና የሰላ ትችት ስላቀረበባቸው የሃንጋሪያዊውን ሥልቶችን በድጋሚ የመጠቀም ድፍረት እንዳልነበረው ይናገራል፡፡ ነገርግን የተሳለቀባቸው ሐሳቦች ግብዓት እንደሆኑት፣ “የእኔ” ለሚለው የአጨዋወት ዘይቤም መሰረት እንደጣሉለት እና በአሰልጣኝነት ሥራው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበራቸው የአደባባይ ምስጢር ስለመሆኑ ይዘረዝራል፡፡ በእርግጥ የፍላቪዮ ኮስታ ጥገናዊ ለውጦችን የማድረግ ችሎታ የጥንቱ ፒራሚድ ፎርሜሽን ላይ ማሻሻያዎች ለማድረግ አዳጋች እንደነበረው ሳይሆን W-M ፎርሜሽን በቀላሉ እደሳዎች ሊደረጉለት እንደሚችል አስመስክሯል፡፡ በፎርሜሽኑ የመሃል ክፍል የሚገኘው <ካሬ> አንዴ ወደ <ፓራሌሎግራም> ከተለወጠ በኋላ ይህንኑ ንድፍ ወደ <ሮምበስ/ዳይመንድ> ቅርጽ ለመቀየር ብዙ የማስተካከያ ርምጃዎች አላስፈለጉም፡፡ ይህ ለውጥ ከተፈጠረ በኋላ ደግሞ የቀረው የ4-2-4 ፎርሜሽን መፈልሰፍ ሆነ፡፡  4-2-4 ፎርሜሽን ከመፈጠሩና ሰፊ ተቀባይነት ከማግኘቱ ቀደም ብሎ ግን ብራዚል የ1950ውን የጣር ዘመን ማለፍ ነበረባት፡፡

ምስል፦1 ዲያጎናል ፎርሜሽን (ፔላ ዲሬይታ)፥ ፍላሚንጎ-1941

ምስል 2፦ ዲያጎናል ፎርሜሽን (ፔላ ኢስኩዌሮኣ)፥ ፍሎሚኔንሴ-1941

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡