ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ወጣት ተጫዋቾቹ ጋር ተለያየ

በዝውውር መስኮቱ ሦስት ተጫዋቾች ማስፈረም የቻሉት ፈረሰኞቹ ባለፉት ዓመታት በታዳጊ ቡድን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይተው ወደ ዋናው ቡድን ካደረጉት ፍሬዘር ካሳ እና ሳሙኤል ተስፋዬ ጋር ተለያይተዋል።

ፍሬዘር ካሳ (ፎቶ በግራ በኩል) ከወጣት ቡድን አድጎ ላለፉት ሦስት ዓመታት በክለቡ እና ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድኑ ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ያሳየ ተጫዋች ነው። በተለይም ቡድኑ በ2009 የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ እና በቻምፒየንስ ሊጉ እስከ ምድብ ጨዋታዎች ሲደርስ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት የቻለ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ አዳዲስ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች መፈረምን ተከትሎ የመሰለፍ እድሉ ተገድቦ ቆይቷል።

ሌላው ከቡድኑ ጋር የተለያየው ላለፉት ሁለት ዓመታት በዋናው ቡድን ቆይታ የነበረው ተከላካዩ ሳሙኤል ተስፋዬ (ፎቶ በቀኝ በኩል) ነው። እንደ ፍሬዘር ሁሉ ከወጣት ቡድን ያደገው ሳሙኤል ብዙም የመጫወት እድል ባያገኝም በዓመቱ መጀመርያ በኦሊምፒክ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት ሃገሩን ወክሎ የተጫወተ ሲሆን ቡድኑ መከላከያን ባሸነፈበት ጨዋታም ግብ ማስቆጠር ችሎ ነበር።

በታዳጊ እግር ኳስ የተሻለ ስራ ከሚሰሩ የኢትዮጵያ ክለቦች የሚጠቀሱት እና በቅርቡም የእግር ኳስ አካዳሚ ባለቤት የሆኑት ፈረሰኞቹ ምንም እንኳ ጥቂት የማይባሉ ተስፈኛ ተጫዋቾች ማውጣት ቢችሉም በዋናው ቡድን ዕድል የተሰጣቸው ግን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡