ሲዳማ ቡናዎች ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ዱባይ ሊያመሩ ነው

ሲዳማ ቡና የቅድመ ውድድር ዝግጅት ለማድረግ እና የአቋም መፈተሻ ውድድር ላይ ተካፋይ ለመሆን ወደ ዱባይ የቡድኑ አባላትን በመያዝ በቅርቡ እንደሚጓዝ ታውቋል።

በ2011 የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተሳካ የውድድር ዓመትን በማሳለፍ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከቻምፒዮኑ መቐለ 70 እንደርታ በመቀጠል ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና ለቀጣዩ ዓመት የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከኢትዮጵያ ውጪ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለማድረግ በዚህ ወር መጨረሻ የቡድኑን ልዑካን በመያዝ ወደ ዱባይ እንደሚያመሩ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ቡድኑ ዘንድሮ በሊጉ ጠንካራ ሆኖ ዓመቱን በሁለተኝነት በማጠናቀቁ አንድ በዱባይ ነዋሪ የሆኑ የክለቡ ደጋፊ ይህንን እድል እንዳመቻቹላቸው የገለፁ ሲሆን ዝግጅት ከማድረግም ባለፈ በዛው በሚዘጋጅ የአቋም መፈተሻ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑም ጨምረው ገልፀዋል። በአሁኑ ሰዓት ተጫዋቾች ፓስፖርት መያዛቸውን በማረጋገጥ እንዲሁም ለሌላቸው አዲስ በማውጣት እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ክለቡ ከአስር ቀናት በኋላ በሀዋሳ ዝግጅቱን እንደሚጀምር ሲጠበቅ ነሐሴ 30 ወደ ስፍራው የሚያመራ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡