ኳታር 2022 | ዋልያዎቹ ለሌሶቶው ጨዋታ በባህር ዳር ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ

በ2022 በኳታር አዘጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከሌሶቶ ጋር ነሐሴ 29 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚጫወቱት ዋሊያዎቹ ዝግጅታቸውን ባልተሟላ መንገድ መስራት ሲጀምሩ የተወሰኑ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር መቀላቀል ጀምረዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ጥሪ ከተደረገላቸው 27 ተጫዋቾች መካከል 12 ተጫዋቾችን በመያዝ ባለተሟላ ሁኔታ ወደ ባህር ዳር በማቅናት ዩኒሰን ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገው በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዳቸውን እየሰሩ ይገኛል። የአዳማው ተስፋኛ አጥቂ ፉአድ ፈረጃ ቡድኑን የተቀላቀለ አዲስ ተጫዋች ሲሆን ክለቦቻቸው በአፍሪካ መድረክ በነበራቸው የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ዝግጅት ያልጀመሩት ግብጠባቂው ጀማል ጣሰው፣ ያሬድ ባዬ፣ ሙጂብ ቃሲም፣ ሐይደር ሸረፋ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲጀምሩ ለግብፁ ክለብ ስሞሀ በመጫወት ላይ የሚገኘው ዑመድ ኡኩሪ ሌላኛው ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለ ተጫዋች ሆኗል።

የፋሲሉ አምሳሉ ጥላሁን በጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የመቀጠሉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን በቅርቡ የጋብቻ ሥነ ስርዓቱን የሚፈፅመው ሱራፌል ዳኛቸውም በጨዋታው መዳረሻ ቀን ጋብቻውን የሚፈፅም በመሆኑ ከብሔራዊ ቡድኑ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል። ለግብፁ ምስር ኤል ማቃሳ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ዛሬ ባህር ዳር በመግባት ነገ ከቡድኑ ጋር ዝግጅት የሚጀምር ሲሆን ቢኒያም በላይ (ከስሪያንስካ/ስዊድን) እና በቅርቡ ለግብፁ ሃራስ ኤል ሆዳድ ፊርማውን ያኖረው ጋቶች ፓኖም ቅዳሜ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የተቀሩት ጥሪ ከደረሳቸው መካከል በኖርዌይ የሚጫወቱት አሚን አስካር እና ዳንኤል ተሰማ እንዲሁም በጀርመን እየተጫወተ የሚገኘው ካሊድ ሙሉጌታ ፌዴሬሽኑ ይፋ ካደረገው ዝርዝር ላይ ቢጠቀሱም ከፓስፖርት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ለጨዋታው የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሌሶቶ ጋር የዛሬ ሳምንት ነሐሴ 29 ቀን 10:00 የሚጫወት ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ