ሰበታ ከተማ ውበቱ አባተን በዋና አሰልጣኝነት መቅጠሩን በጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቀ

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ብቅ ያለው ሰበታ ከተማ ውበቱ አባተን አዲስ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙንና አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ መቀላቀሉን አስመልክቶ ዛሬ 4:00 ላይ ዓለምገና ከተማ በሚገኘው ዓለም ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

3:00 ላይ ይጀምራል በተባለው እና በአንድ ሰዓት ዘግይቶ በጀመረው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አዲሱን አሰልጣኝ ጨምሮ የሰበታ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን ኃላፊ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ኦብሳ ለገሰ፣ ስራ አስኪያጁ አቶ ዓለማየሁ ምንዳን ጨምሮ የክለቡ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ተጫዋቾች እና ጋዜጠኞች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ሲሆኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ ስለ አዲሱ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አመራረጥ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ “አሰልጣኝ ውበቱ ከፍተኛ ልምድ አለው። እኛም እሱን በመምረጣችን ደስተኛ ነን። የካፍ A ላይሰንስ ባለቤት እና እስካሁን በፕሪምየር ሊጉ ተፎካካሪ ቡድን እየሰራ በመሆኑ ለኛም ክለብ አስፈላጊነቱን በሚገባ ስለተረዳን ነው ወደ እኛ ያመጣነው።” ብለዋል።

አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ጥሩ ቡድን እንገነባለንም ብለዋል። “እኔ ወደዚህ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ። ከነሱ ጥያቄው ሲመጣ መጀመሪያ ሳልቀበል ቀረው። ያም የሆነው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተስማምቼ ስለነበረ ያ ሳይሆን በመቅረቱ ከነበረብኝ የግል ችግር የተነሳ ሰበታ ለአዲስ አበባም ቅርብ በመሆኑም ምርጫዬ አድርጌያለሁ። በዚህም ደስተኛ ነኝ፤ ስኬታማ ጊዜንም አሳልፋለሁ።” ብለዋል።

በመቀጠል በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን የክለቡ አመራሮች እና አዲሱ አሰልጣኝ ምላሽም ሰጥተዋል፡፡ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ክለቡ ያስፈረማቸው አዳዲስ ተጫዋቾች የረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው ናቸው። ይህ ለታዳጊዎች ቦታን አይጋፋም ወይ? የስመጥር ተጫዋቾች መበራከትስ ለቡድኑ ነፃነት ምን ያህል ጠቃሚ ነው? የሚሉ ሲገኙበት በዚሁ ላይ አሰልጣኙ በሚታወቁበት የታዳጊ ተጫዋች ምልመላ ሰበታ ተግባራዊ ለማድረግ ምን ያህል ንቁ ነው? ክለቡ ለዘንድሮው ዓመት እቅዱ ምንድነው? በሜዳ ላይ እየታየ ካለው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ጋር በተያያዘስ ክለቡ ያስቀመጠው ዕቅድ ይኖር ይሆን? የሚሉ እንዲሁም የሰበታ ሜዳ ለአሰልጣኙ አጨዋወት ምቹ አይደለም በዚህስ ላይ ምን አሰባችሁ? የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር የተያያዘ እና ከጋዜጠኞች ከተነሱት ጥያቄዎች በተጨማሪም የክለቡ አመራሮች የክለቡ እቅድ እና በውድድር ዓመቱ ጉዞ ያለው ሂደት በምላሻቸው አካተዋል፡፡

አስቀድመው ምላሽ መስጠት የጀመሩት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ሲሆኑ ክለቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች አጠር ያለ መልስን ሰጥተዋል። “አሰልጣኙ ከኛ ጋር ሁለት ዓመት ነው የውል ስምምነታቸው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ታዳጊን መሠረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን እንቀርፃለን። ለአሁኑ ግን ክለቡን በሊጉ መቆየት እንዲችሉ ልምድ ያላቸው መካተታቸው ቡድኑ ተፎካካሪ እንዲሆን ያስችላሉ። ነገር ግን አሰልጣኙ በክለቡ በሚቆዩበት ወቅት በከተማችን አስር ቀበሌ አለ። በያንዳንዱ ቀበሌ አንዳንድ ፕሮጀክት እንገነባለን፤ ያን አድርገን በቀጣዩ አመታት ጥሩ ወጣቶችን እናወጣለን።” ብለዋል። ስራ አስኪያጁ አክለውም ከታዳጊ ልጆች በተጨማሪ በሴቶች ላይ ትኩረት እንሰጣለን ያሉ ሲሆን በቅርቡ ደጋፊ ማህበር ለማቋቋም በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል።

በመቀጠል ምላሽን የሰጡት የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ኦብሳ ሲሆኑ ከዲሲፕሊን ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ክለቡ አርዓያ መሆን እንዳለበት ገልፀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለሁሉም የክለቡ ደጋፊዎች ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ክለቡ ራሱን ችሎ ከገንዘብ ጥገኝነት እንዲላቀቅ አንዳንድ ጥናቶች እየተሰሩ እንደሆነ እና በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ ብለዋል። “ክለቡን በሰው ኃይል ለማጠናከር እየተንቀሳቀስን ነው። ይህ ክለብ በመንግሥት ካዝና ነው የሚተዳደረው። በቀጣይ ግን በራሱ መቆም እንዲችል የአምስት ዓመት ዕቅድ እና ጥናት የያዝን ሲሆን የራሱ ህንፃ፤ የገበያ ማዕከል ያለው ዘመናዊ ኮምፕሌክስ ገንብተን ራሱን የቻለ እና በአፍሪካ ተፎካካሪ ክለብ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል።” ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ከአሳዳጊው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር በምን እንደተለያዩ ሲናገሩ “አሰልጣኝ ክፍሌ የክለባችን ባለውለታ ናቸው። ሁሌም ቢሆን በኛ በኩል ምስጋናችን የማይቋረጥ ነው። ከአሰልጣኙ ጋር መቀጠል ያልፈለግነው ግን ልምድ ያለው፣ ከስጋት ነፃ ሊያደርገን የሚችል አሰልጣኝ በመፈለጋችን እና በሁሉም ነገር እንደ አዲስ ወደ ውድድር መግባት ስለፈለግን ብቻ ነው ከአሰልጣኙ ጋር ላንቀጥል የቻልነው።” ብለዋል። ዘንድሮ በሊጉ እንዲቆይ ለማድረግ እንደሚሰራ እና በቀጣዩ ዓመት ግን ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን እንደሚኖርም ቃል ገብተዋል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ወደ ክለቡ በመቀላቀላቸው በድጋሚ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ያቀዱትን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። አዲስ ከመጡ ተጫዋቾች ጋር ለተነሳው ጥያቄም መልስ ሰጥተዋል። “ክለቡን ተፎካካሪ ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ ሰው የሚያየው እና ራሱን ቢዚ ሊያደርግ የሚችልበት ቡድን ለመገንባት አስቤያለሁ። ለዚህም ለእኔ አጨዋወት የሚሆኑ ከዚህ በፊትም አብረውኝ የሰሩ ተጫዋቾችን አምጥቻለሁ። ይህን ያደረኩትም ስለማውቃቸው አብሬ ስለሰራሁም ጭምር ነው። እኚህ ተጫዋቾች የመጡት እኔ አምኜባቸው በእኔ ፍላጎት የመጡ ናቸው። ለምን ከተባለ በዚህ ሰዓት ውጤት መያዝ አስፈላጊው ጉዳይ ነው። ውጤት ለማምጣት ደግሞ ቶሎ የኔን አጨዋወት የሚረዱ፤ ሲኒየር በመሆናቸውም መፍትሔ ከነሱ እንደሚገኝ ስላሰብኩ የመጡ ስለሆኑ ምንም ችግር አይኖርም።” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ ቀጥለውም አስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ያመጣው ሰበታ ከተማ አስር ተጫዋቾችን ለመተካት ደግሞ ታዳጊዎች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል። “ወጣቶች ላይ ለመስራት ጊዜ ይፈልጋል። እኔም ክለቡ በሚከተለው የወጣቶች ልማት ላይ እሳተፋለሁ። ከዋናው ቡድን አሰልጣኝቴ ባለፈ ወደታች ወርጄ ለመስራት እሞክራለሁ።”

ከሜዳ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች አሰልጣኝ ውበቱ “እኔ እዚህ ክለብ ስመጣ በቅድሚያ ሜዳው መስተካከል አለበት የሚል ነበር ከአመራሮቹ ጋር ያደረግኩት ንግግር። ለአንድ ቡድን ተጫዋቾች እና ሜዳ ወሳኝ ነው። እኔ ለምከተለውም አጨዋወትም ጭምር። እኔም ሜዳው እየተሰራ መሆኑን በማየቴ ነው ልፈርም የቻልኩት።” ያሉት አሰልጣኙ ጠንካራ ቡድን ለመገንባት ሁሉም ከጎኑ እንዲሆን የገለፁ ሲሆን በፋሲል ቆይታቸው ደጋፊዎች ያስመሰከሩትን የስፖርታዊ ጨዋነት ሰበታ ላይ መደገም አለበት የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከተደረጉት ጥያቄ እና መልስ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በይፋ የክለቡ አሰልጣኝ ተደርገው መሾማቸው በዕለቱ በነበረው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት የተገለፀ ሲሆን አሰልጣኙም የሁለት ዓመት የውል ስምምነትን ፈፅመዋል። የአዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች ትውውቅ ከተደረገ በኋላም መርሐ ግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ