ቻን 2020| የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ልታደርግ ነው


በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ሁለተኛ ዙር ማጣርያ ኢትዮጵያን የምትገጥመው ሩዋንዳ ለጨዋታው ወደ መቐለ ከማምራቷ በፊት የአቋም መለኪያ ታደርጋለች።

ከአራት ቀናት በፊት ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው በአሰልጣኝ ቪሰንት ማሻሚ እየተመሩ ዝግጅት የጀመሩት ሩዋንዳዎች ከሁለት ቀናት በኋላ በቻን ውድድሮች ጥንካሬዋን ያሳየችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ይገጥማሉ። በስታደ ኪጋሊ ልምምድ በማድረግ ላይ የሚገኙት ‘አማቩቢ’ዎቹ ከወዳጅነት ጨዋታው ቀጥሎ ባለው ቀን አዲስ አበባ ገብተው በዛው ቀን ጨዋታው ወደሚደረግበት መቐለ እንደሚያመሩ ለማወቅ ተችሏል።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በቻን ውድድር ማጣርያ ለሦስተኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን የመጀመርያውን (2014) ኢትዮጵያ፤ ቀጣዩን (2018) ደግሞ ሩዋንዳ አሸንፈው ለውድድሩ ማለፋቸው ይታወሳል። በተለይም በ2018ቱ ማጣርያ ሩዋንዳ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኤሩክ ሩታንጋ፣ ሙሐጅር ሐኪዝማና እና ዓብዲ ቢራማሂሬ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3-2 አሸንፋ መመለሷ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ