“ኢትዮ ኤሌክትሪክ አይፈርስም” አቶ ኢሳይያስ ደንድር

ቡድኑን ሊያፈርስ እንደሚችል ሲነገር የሰነበተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንደ ክለብ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳይያስ ደንድር ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በስኬት ያሸበረቀ ታሪክ ካላቸው ክለቦች አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌትሪክ እግርኳስ ክለብ በውስጣዊ እና በውጫዊ ችግሮች ምክንያት የቀደመ ስሙን እየለቀቀ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በ2010 የውድድር ዘመን ወደ ታችኛው ሊግ በመውረድ በከፍተኛ ሊግ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2012 የውድድር ዘመን በ24 ቡድኖች እና በሁለት ምድቦች ተከፍሎ በማዋቀሩ ክለቡ “እኛን ማካተት ይገባዋል” ሲል ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አቤቱታውን በማቅረብ ተገቢውን ምላሽ የማያገኝ ከሆነም በቅርቡ አቋሙን እንደሚያሳውቅ መግለፁ በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ ክለቡ ሊፈርስ ይችል ይሆን? የሚል ስጋት ፈጥሯል። በዚህ ጉዳይ ላይም የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ደንድር ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን አስተያየት ሰጥተዋል።

” ኢትዮ ኤሌክትሪክ ታሪካዊ ክለብ ነው። እንዲህ በቀላሉ የሚፈረስ ክለብ አይደለም። በፌዴሬሽኑ ብዙ በደሎች እየተፈፀሙብን ለምንጠይቃቸው ፍትሀዊ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሾች እያጣን እዚህ ደርሰናል። በቀጣይም ህጉን በተከተለ መንገድ እስከሚመለከታቸወ አካላት ድረስ ጉዳዮቻችንን በመያዝ መፍትሄ ለማግኘት እንቀጥላለን እንጂ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አይፈርስም። እንዲያውም በሁሉም የእድሜ እርከን ለዘንድሮ የውድድር ዓመት በተሻለ ሁኔታ ተጠናክረን እንቀርባለን። ዋናው የወንዶቹ ቡድን ከነገ ጀምሮ ወደ ሀዋሳ ከተማ በመጓዝ ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል” በማለት የክለቡን አቋም ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ