መቐለ 70 እንደርታ ጋናዊውን ተከላካይ ለማስፈረም ተስማማ

ከጥቂት ቀናት በፊት የክብሮም አፅብሃ እና ዐቢይ ተወልደን ዝውውር ያጠናቀቁት መቐለ 70 እንደርታዎች ጋናዊው ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

የ25 ዓመቱ ተከላካይ በሃገሩ ክለብ ናንያ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረ ሲሆን በደቡብ አፍሪካው አያክስ ኬፕ ታውን የሁለት ዓመት ቆይታ እንዲሁም የቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ የወራት ቆይታ አድርጎ ነበር በ2009 ክረምት ለሀዋሳ ከተማ ፊርማውን ያኖረው።

ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ሦስት ጨዋታዎች ማድረግ የቻለው ይህ ወጣት ተከላካይ ለሃገሩ ጋና በአራት የብሄራዊ ቡድን እርከኖች መጫወት የቻለ ሲሆን ለ20 ዓመት ብሄራዊ ቡድንም በርካታ ጨዋታዎችን በአምበልነት መርቷል። በ2013 ሃገሩ ጋና በቱርክ ከ20 ዓመት ዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃ ስትይዝም የቡድኑ አባል አባል ነበር።

በሌላ ዜና ላለፉት ቀናት ከክለቡ ጋር ልምምድ ጀምሮ የነበረው እና በቅርቡ ይፈርማል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አማካዩ አዲስ ህንፃ በአንዳንድ ጉዳዮች ከክለቡ ጋር መስማማት ባለመቻሉ ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል።

ቡድኑ ከዚህ ቀደም ለሙሳ ካማራ፣ ሙሳ ዳኦ፣ ሳሙኤል አቤኩ እና ጎይትኦም ነጋ የሙከራ ዕድል ሰጥቶ ተጫዋቾቹ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌን ማሳመን ባለመቻላቸው ሳይፈርሙ መቅረታቸው ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ