የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ውሎ…

(መረጃው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው)

ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ወሎ ሰፈር በሚገኘው የተቋሙ አዲስ ሕንጻ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ከጠዋቱ 4ሰዓት እሰከ ምሽቱ 1ሰዓት አካሂደዋል፡፡ 

በ2011ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጣው አመራር በቆይታው ምንም ጉዳዮች ተሰሩ ምንስ ሳይሰራ ቀረ፤ እንዲሁም ስራዎችን በምን ደረጃ ሲከታተል ቆየ በሚል አጠቃላይ የፌዴሬሽኑ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ቀደም በተቋሙ የታዩ ክፍተቶች በምን ደረጃ መስተካከል ይኖርባቸዋል፤ በስራ አስፈጻሚው መካከል የነበረው አለመናበብ እና በቀጣይ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እንዲሁም የግል ግምገማ በማድረግ የሚከተሉት ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቀደመው መልኩ በ16 ቡድኖች መካከል እንዲካሄድ ውድድሩ በምን አግባብ መመራት እንዳለበት ከክለቦች ጋር በቅርብ ቀን ውይይት እንዲካሄድ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ በአንድ የውድድር ዘመን ሁለት ጊዜ ፎርፌ ለተጋጣሚ ቡድኖች የሰጠ ቡድን ከውድድር ይሰረዛል ይላል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ሁለት ጊዜ በወጣለት ፕሮግራም አለመገኘቱን በወቅቱ ጨዋታውን ከመሩት ዳኞች እና የጫወታ ታዛቢዎች ሪፖርት ተመልክቶ የሊግ ኮሚቴ ውጤቱን ማጽደቁ ትክክል ቢሆንም በቀጣይ በዲሲፕሊን ኮሚቴ መወሰን ያለባቸው ውሳኔዎችን የውድድር ክፍል በወቅቱ ባለማሳወቁ ውሳኔው ሂደት ያልጠበቀ እንዲሆን አድርጎታል፤ ስህተቱን በፈጠረው ሰራተኛ ላይ የዲሲፕሊን ቅጣት እንዲተላለፍበት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊግ እንዲቆይ እና በ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንዲወዳደር ተወስኗል፡፡

በአንደኛ ሊግ ተሳታፊ የነበረው ቦሌ ገርጂ እግር ኳስ ክለብ በጸጥታ ችግር ቡድኑ ወደ ጨዋታ ስፍራ መጓዝ ባለመቻሉ የተሰጠው ፎርፌ ቡድኑ አንዲሰረዝ ምክንያት እንደነበር ይታወቃል ሆኖም ውድድር ክፍል ላይ በነበረው የአሰራር ክፍተት ቡድኑ አለመጓዙን ስራ አስፈጻሚው ስለተረዳ ቡድኑ ላይ የተሰጠው ውሳኔ እንዲሰረዝ እና በአንደኛ ሊግ እንዲወዳደር ተወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለኳታር የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ሌሴቶ ሲያቀና ላጋጠመው እንግልት ምክንያት የሆኑ ሰራተኞች በጽ/ቤቱ በኩል በሰራተኞች አስተዳደር በዲሲፕሊን እንዲጠየቁ እንዲሁም የጽ/ቤት ኃላፊው የመጀመሪያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ አንዲሰጣቸው ወሳኔ ተላልፏል፡፡