ደቡብ ፖሊስ ሦስት ወጣት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በፌዴሬሽኑ የፎርማት ለውጥ የተነሳ አዲስ ፈርመው ከነበሩ ተጫዋቾች ጋር እንደሚለያይ የሚጠበቀው ደቡብ ፖሊስ ሦስት አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ አምጥቷል፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ የታዳጊ ቡድኑ የተገኘው ዮሐንስ ዘገየ ወደ ቢጫ ለባሾቹ ቤት ያመራ ተጫዋች ነው፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ካደገ በኃላ በመጀመሪያው ዓመት ጅማሮ ተስፋ ሰጪ ጊዜን ያሳለፈው ዮሀንስ በሒደት ብዙም መሰለፍ ዕድል ባለማግኘቱ ወደ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተጉዞ የአንድ ዓመት ቆይታን አድርጎ ነው ወደ ፖሊስ ያመራው፡፡

ይታጀብ ገብረማርያም ሌላኛው አዲስ ፈራሚ ነው፡፡ ከመከላከያ የተስፋ ቡድን የተገኘው ይህ የፊት እና የመስመር አጥቂ ባለፈው ዓመት በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ከቻለ በኋላ በክለቡ ጥቂት ጨዋታዎች ላይ ዕድልን ያገኘ ቢሆንም የውል ጊዜ እየቀረው ከመከላከያ ተለያይቶ ፖሊስን ተቀላቅሏል፡፡

እንደ ይታጀብ ሁሉ ከመከላከያ ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች አብነት ይግለጡ ሆኗል፡፡ ከጦሩ ታዳጊ ቡድን የተገኘውና በዋናው ቡድን ቆይታ የነበረው ይህ ተጫዋች በተከላካይ ስፍራ ላይ ይጫወታል።

በተያያዘ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረው ዩጋንዳዊው አማካይ ኢቫን ሳካዛ በትላንትናው ዕለት ለአንድ ዓመት ለክለቡ ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ