ሪፖርት | የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በወዳጅነት ጨዋታ ተሸነፈ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዩጋንዳን በወዳጅነት ጨዋታ ገጥሞ 1-0 ተሸንፏል።

በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ብዙ የጠሩ የግበ ማግባት አጋጣሚዎች ሳይስተዋሉበት ተጠናቋል። በአንፃራዊነት ፍትጊያዎች እና አካላዊ ጉሽሚያዎች በበዙበት የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ተጋባዦቹ ዩጋንዳዎች ተሽለው ሲንቀሳቀሱ ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያዎች ደግሞ ተዳክመው ታይተዋል።

ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ በፍፁም አለሙ አማካኝነት የግብ ሙከራ በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩት ዋሊያዎቹ ሙከራቸው በግብ ጠባቂው ዴኒስ ኦኒያንጎ አማካኝነት መክኖባቸዋል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ዩጋንዳዎ በ7ኛው ደቂቃ ጥሩ ሙከራ ሰንዝረው መክኖባቸዋል። በዚህ ደቂቃ በመስመር አጨዋወት ወደ ግብ የደረሱት ተጋባዦቹ በሉዋጋ ኪዚቶ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረዋል። በ14ኛው ደቂቃ ዳግም ወደ ዋሊያዎቹ የግብ ክልል የደረሱት ዩጋንዳዎች በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ሉማላ አብዱ አማካኝነት ሙከራ አድርገዋል።

ከአምስት ደቂቃ በኋላ በኢትዮጵያ የግብ ክልል አካባቢ የቅጣት ምት ያገኙት ክሬንሶች አጋጣሚውን ወደ ግብነት ቀይረው መሪ ሆነዋል። የቅጣት ምቱ ሲሻማ ብቻውን ቆሞ የነበረወ ዮሴፍ ኦቻያ ለኦክዊ ኢምኑኤል አሻምቶለት ግቡ በግምባር ተቆጥሯል።

ሳይታሰብ ግብ ያስተናገዱት ዋሊያዎቹ በ27ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው በሞከረው የቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር ጥረው ነበረ። ከደቂቃ በኋላም ዋሊያዎቹ ለሙጂብ ቃሲም የተሰነጠቀን ረጅም ኳስ ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ግብ ጠባቂው ዴኒስ ኦኒያንጎ ወቶ አድኖባቸዋል። በክፍት ጨዋታ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር የተሳናቸው የአሰልጣኝ አብርሃም ተጨዋቾች በ35 እና 38ኛው ደቂቃ አዲስ ግዳይ እና ሱራፌል ዳኛቸው በሞከሯቸው የቅጣት ምቶች የአቻነት ግብ ፈልገዋል።

በፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮች ጨዋታቸውን የቀጠሉት ክሬንሶች በ40ኛው ደቂቃ ሉማላ አብዱ በመታው ነገር ግን ደስታ ደሙ እና ለዓለም ብርሃኑ ተባብረው ባወጡት ኳስ መሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ ተቃርበው ነበረ። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይስተዋልበት ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በአንፃራዊነት በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው ለመቅረብ የጣሩት ዋሊያዎቹ በተሻለ የጨዋታ ፍላጎት ጨዋታቸውን አከናውነዋል። በተቃራኒው በመጀመሪያው አጋማሽ መሪ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል የተጓዙት ዩጋንዳዎች ያገኙትን የማሸነፊያ እድል አሳልፎ ላለመስጠት ተንቀሳቅሰዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ዩጋንዳዎች በግራ መስመር በመሄድ ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው ለዓለም አድኖባቸዋል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ዩጋንዳዎች የግብ ክልል የደረሱት ሃይደር ሸረፋ እና ፍፁም ዓለሙ አጋጣሚውን ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በ55ኛው ደቂቃ ወደ ዋሊያዎቹ የግብ ክልል የደረሱት የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ኢማኑኤል አርኖልድ አኪዊ እና ሉዋጋ ኪዚቶ ተቀባብለው ነገር ግን ሉዋጋ ኪዚቶ ባመከነው የመልሶ ማጥቃት ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር።

ከ55-70ኛው ደቂቃ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ዋሊያዎቹ ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቧቸው ተጨዋቾች ታግዘው ወደ ግብ ለመድረስ ቢጥሩም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር ተስኗቸው ታይቷል። በተለይ አሰልጣኙ የአማካኝ መስመር ተጨዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ ቡድኑ ተረጋግቶ ኳስን ወደ ፊት ለማድረስ ጥሯል።

የመጨረሻው የሁለተኛው አጋማሽ ሙከራ በ55ኛው ደቂቃ በዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድነን አማካኝነት ከተደረገ በኋላ ጨዋታው ሙከራ ያስተናገደው በ89ኛው ደቂቃ ነው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በቀኝ መስመር ወደ ዩጋንዳ የግብ ክልል ያመሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አዲስ ግዳይ አሻምቶት ነገር ግን ማንም ሳይደርስበት በቀረው እድል ወደ ግብ ቀርበው ነበረ። ከዚህች ሙከራ በተጨማሪ ባለቀ ሰዓት ዋለሊያዎቹ ጥሩ የግብ ማግባት እድል ፈጥረው ነበረ። ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት አስቻለው ታመነ አሻምቶት ፍቃዱ ወርቁ በግምባሩ ቢሞክረውም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በዩጋንዳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በባህር ዳር ስታዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ