ስሑል ሽረ ከሁለት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ሲለያይ የአምስት ነባሮችን ውል አራዝሟል

ከዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ እና ብሩክ ተሾመ ጋር በስምምነት የተለያዩት ሽረዎች የአምስት ነባር ተጫዋቾቻቸውን ቆይታ አራዝመዋል።

ቀደም ብለው የአሰልጣኝ ሳምሶን አየለን ውል በማራዘም በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ስሑል ሽረዎች በአንፃሩ ከሌሎች ተጫዋቾቻቸው ጋር ደግሞ ተለያይተዋል። ከቡድኑ ጋር በስምምነት የተለያዩት ሁለቱ ተጫዋቾች ባለፈው ዓመት መጀመርያ አዲስ አበባ ከተማን ለቆ ስሑል ሽረን በመቀላቀል ቡድኑን በአምበልነት የመራው የቀድሞው የሐረር ቢራ እና አዳማ ከተማ ተከላካይ ዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ እና ከደደቢት እና ጅማ አባጅፋር ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው በመሀል ተከላካይነት እንዲሁም በአማካይ ስፍራ መጫወት የሚችለው ብሩክ ተሾመ ናቸው።

ከዚህ በተቃራኒው ክለቡ ከሌሎች አምስት ተጨዋቾቹ ጋር አብሮ ለመቆየት በመስምማት ውላቸውን አራዝሟል። በክለቡ መቆየታቸው ነገር የተረጋገጠው ተጫዋቾችም ነፃነት ገብረመድህን ፣ ተክላይ በርኸ ፣ ዋልታ አንደይ ፣ ክብሮም ብርሃነ እና ጌታቸው ተስፋይ ሆነዋል። በስሑል ሽረ ለመቆየት የተስማሙት አብዛኞቹ ተጫዋቾች የሁለተኛው ቡድን ውጤቶች ሲሆኑ ክለቡን ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ