አዳማ ከተማ የሴቶች ቡድን አሰልጣኙን ውል አራዝሟል

የዐምናው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አሸናፊ አዳማ ከተማ የአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዘመ፡፡

የቀድሞው የአዳማ ከተማ፣ ሙገር ሲሚንቶ እንዲሁም የደብረብርሃን ከተማ ተጫዋች ሳሙኤል የአሰልጣኝነት ህይወቱን ጅማሮ ያደረገው በአዳማ ከተማ የተስፋ ቡድን ሲሆን ላለፉት አራት ዓመታት በአዳማ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡

በተስፈኛው አሰልጣኝ የሚመሩት አዳማዎች በወጣቶች በተገነባው ቡድናቸው በተለይም ከ2009 የውድድር ጀምሮ በሊጉ አናት ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው መቅረብ ችለዋል፤ በ2009 የውድድር ዘመንም ቡድኑ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የወቅቱ ኃያላን የነበሩትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና ደደቢትን እስመጨረሻው በመገዳደር ሦስተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ሲችሉ ባሳለፍነው ዓመት ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ቻምፒዮን እንዲሆኑ ማስቻሉ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ የክለቡ ዜና ከዚህ ቀደም የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቁ በመጪው እሁድ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በአዳማ ከተማ የሚጀምሩ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ