በዓለምነህ ግርማ እና መከላከያ ጉዳይ ዙሪያ ፌዴሬሽኑ ውሳኔን ሰጠ

በመከላከያ ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት እየቀረው በክለቡ ለመሰናበት መገደዱን በመግለፅ ለፌዴሬሽኑ ቅሬታ ያቀረበው ዓለምነህ ግርማ ውሳኔ አግኝቷል፡፡

በ2010 የውድድር ዘመን ክረምት ወልዋሎን በመልቀቅ ወደ መከላከያ ያመራው የግራ ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዓለምነህ ዐምና በጦሩ ቤት የመጀመሪያ የኮንትራት ዓመቱን ከቆየ በኋላ ግን ዘንድሮ ቀሪ የአንድ ዓመት የውል ጊዜ እያለው ከመከላከያ እንደተሰናበተ ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አቤቱታውን ገልጿል። ተጫዋቹ በአቤቱታው “ክለቡ ደውሎልኝ ለዝግጅት ወደ አዳማ ሄጄ ብቀላቀልም አሰልጣኙ ደብዳቤ ካላመጣህ አትገባም ስላሉኝ ደብዳቤ ለማምጣት ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ የጠየቅኩ ቢሆንም ክለቡ ያን ሊያደርግ አልቻለም። በተደጋጋሚ ብጠይቃቸውም ምላሽ ላገኝ አልቻልኩም። ክለቡ ይባስ ብሎ ወደ ዝግጅት አልገባህም ብሎ ደብዳቤ ፅፎብኛል። ይሄ ደግሞ በራሴ ላይ የሞራል ውድቀትን አስከትሎብኛል፤ ውል እያለኝም ክለቡ በተለያዩ ምክንያቶች እያጉላላኝ ነው።” በማለት ባስገባው ቅሬታ መሠረት የፌድሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ጉዳዩን ከመመረመረ በኃላ በመከላከያ ክለብ ላይ ውሳኔን አሳልፏል።

ፌዴሬሽኑ በመመሪያው አንቀፅ 89 ንዑስ አንቀስ 1 መሠረት

1) ለተጫዋቾቹ ያልተከፈለው ደመወዝ መከላከያ ስፖርት ክለብ ይህ ውሳኔ በደረሰው 7 ቀን ውስጥ እንዲከፈለው። ክለቡ ውሳኔውን የማይፈፅም ከሆነም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ

2) ክለቡ ይህ ውሳኔ በደረሰው በ7 ቀን ውስጥ ተጫዋቹን ወደ ስራ እንዲመልሰው፤ ያ ካልሆነ ደግሞ እስከ ውል ማብቂያው ድረስ ያለውን ደመወዝ ውሳኔው በደረሰው 7 ቀን ውስጥ ተፈፃሚ በማድረግ ለፌዴሬሽኑ እንዲያሳውቅ።

የፌደሬሽኑ ውሳኔ ዝርዝር 👇


© ሶከር ኢትዮጵያ