በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ዝግጅት ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

በመጪው ረቡዕ በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ላይ ለመካፋል ወደ ሥፍራው በሚያቀናው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዙርያ ዛሬ ከሰዓት በኢትዮጵያ ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ በመግለጫው ላይም የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውና የቡድኑ አምበል ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ተገኝተዋል፡፡

በመግለጫው የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው

አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው

ስለነበራቸው ዝግጅት

“ቡድኑ ልምምድ ከጀመረ 8 ቀን አስቆጥሯል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው የእኔ ቅጥርም የተፈፀመው ካለው የጊዜ ጥበት የተነሳ እንደከዚህ ቀደሙ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ጥሪ ማድረግ አልፈለግንም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገን ጠንካራ የቅንጅት ስራ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ የተጫዋቾች በክለብ በቂ ልምምድ አለማድረግና ተጫዋቾች ከውድድር የራቁ መሆን ችግር ፈጥሮብናል፤ በአጠቃላይ ከነበረው አጭር ጊዜ አንፃር በተጫዋቾች አእምሮ ላይ ከፍተኛ ስራ ለመስራት ጥረት ተደርጓል በተመሳሳይም ከቀደሙ ብሔራዊ ቡድኖች ልምድ ለመውሰድ በሜዳ ላይ እንዲሁም በክፍል ውስጥ በዲፓርትመንት ከፋፍለን ስራዎችን ለመስራት ሞክረናል፡፡”

ከሴካፋ ጉዟቸው ለማሳከት ስላቀዱት

“ከነበረው የዝግጅት ጊዜ ማጠርና ተጫዋቾቹ ከውድድር ርቀው ከመቆየታቸው የተነሳ ውጤት ዋንጫ እናመጣለን ወይም ይህን ደረጃ ይዘን እንጨርሳለን ብዬ መጥቀስ አልፈልግም ፤ በቀጣይ ላለብን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት መሠረት የምንጥልበት ውድድር ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡”

“በሴካፋው ውድድር ላይ በስብስቡ የተካተቱ ተጫዋቾችን በአግባቡ በመግምገም በቀጣይ ላሉብን ጨዋታዎች ሌሎች ያልተመረጡ የተዘለሉ ተጫዋቾችን በማካተት ተወዳዳሪ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት እቅድ ይዘናል፡፡”

“ላረጋግጥላችሁ የምወደው በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑን ማሳለፍ ይጠበቅብኛል ፤ በእቅዴ መሠረት ይህን የማላሳካ ከሆነ ቃል የምገባላችሁ ነገር ቢኖር በነጋታው በገዛ ፍቃዴ ስራዬን የምለቅ ይሆናል፡፡”

ስለ ቅጥር ሁኔታው

” እግርኳስ በባህሪው በሂደት ውስጥ ተረጋግተህ የሚሰራ ስራ ነው ፤ ምንም እንኳን ጊዜው አጭር ቢሆንም ሀገሬን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ስላለኝና በብዛት ተጫዋቾቹን ስለማውቃቸሁ የተቻለኝን ለሀገሬ ለማበርከት ጥሬውን ተቀብያለሁ፡፡”

ብርቱካን ገ/ክርስቶስ

“የአንድ ሳምንት ልምምድ በክፍልና በሜዳ ሰርተናል በአሁኑ ወቅት ጥሩ የመነቃቃት ስሜት ላይ እንገኛለን፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: