‘እግርኳስ ለሠላም’ በሚል መርህ የተዘጋጀው ስልጠና ተጠናቀቀ

በፓክት ኢትዮጵያ ፣ ዩኤስ ኤይድ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የጋራ ትብብር ለአንድ ሳምንት በሱሉልታ ከተማ ሲካሄድ የነበረው ‘እግር ኳስ ለሠላም’ በሚል መርህ የተዘጋጀው ስልጠና እና የምክክር መድረክ ትላንት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እየታየ ያለውን የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ለመፍታት በማሰብ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ቢሆንም በዓይነቱ ካለፉት ስልጠናዎች ለየት ባለ መልኩ ‘እግር ኳስ ለሰላም’ በሚል መርህ ከጥቅምት 30 እስከ ኅዳር 5 በሱሉልታ ከተማ ሲደረግ የነበረው ስልጠና እና የምክክር ፕሮግራም ዛሬ ተቋጭቷል፡፡

በአሜሪካው ዩኤስ ኤይድ እና ፓክት ኢትዮጵያ አዘጋጅነት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በአስተባባሪነት በተሳተፈበት በዚህ ስልጠና የክለብ አመራሮች እና በዋናነት የክለቦች ደጋፊዎች ተሳታፊ ነበሩ። ስልጠናው በክፍል ውስጥ እና በተግባርም ጭምር የተደገፈ ሲሆን እግር ኳስን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዴት መምራት ይቻላል በሚል እና እየታዩ ያሉ ቅጥ ያጡ የሜዳ ላይ አሳፋሪ ድርጊቶችን መቅረፍ በሚያስችሉ መንገዶች ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ ነበር።

በስልጠናው ወቅት እንደተገለፀው እግርኳሱ ላይ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት እየተስፋፋ የመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በዋናነት የፖለቲካ እና ዘረኝነት ዘልቀው ወደ ስፖርቱ የመግባቸው ውጤት እንደሆነ ሲጠቆም በቀጣይ ግን ጉዳዩ በአንድነት እና በወንድማማችነት መንፈስ በስፖርት ዓይን ብቻ ሊታይ እንደሚገባው ተገልጿል። ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበትም ተመልክቷል። ከስልጠናው ባሻገር በነበሩት የውይይት መድረኮች ክለቦች የዕርስ በዕርስ ግንኙነታቸውን ማስፋት በሚችሉበት መንገድ ዙሪያ ያተኮሩ ፕሮግራሞችም ተካተው ነበር።

በመዝጊያው ዕለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የስልጠናውን ሙሉ ወጪ በመቻል ያዘጋጁት የዩኤስ ኤይድ አስተባባሪ አቶ ቢኒያም አካሉ እና የፓክት ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ሙላት እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ስነስርአቱ ተደርጓል፡፡ ስልጠናውን ለተከታተሉ የሰርተፊኬት ሽልማት ከተሰጠ በኃላ ‘መቐለ እና ፋሲል በተጨማሪም ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻን አንድ ማድረግ አለብን’ በሚል በድራማ መልክ የማቀራረብ ስራን የሚያሳይ ትዕይንት ከቀረበ በኃላ ችግሩን ለመፍታት ቃልም ተገብቷል፡፡

የዩኤስ ኤይድ እና የፓክት ዳይሬክተር እግርኳሱን ወደ ሰላም ለማምጣት በሚሰሩ ስራዎች ላይ የማያቋርጥ ዕገዛን እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራም ሁሉም ሰልጣኞች ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ታች በማውረድ በትምህርት ቤቶች ፣ ወረዳዎች ፣ ዞኖች እና ከተሞች እግርኳስ ፍቅር እና ሰላም ብቻ መሆኑን በመስረዳት እና ተግባራዊ በማድረግ ማካፈል እንዳለባቸው የተናገሩ ሲሆን በመጨረሻ የስልጠናው ተካፋዮች ሰላምን የሚያሳይ ምስል የሰፈረባቸው ስጦታዎችን ለዕለቱ ዕንግዶች እና ስልጠናው ለተካሄደበት ያያ ቪሌጅ ካበረከቱ በኃላ ፕሮግራሙ ተዘግቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ