ከፍተኛ ሊግ | የዲስፕሊን ኮሚቴ በመድን ተጫዋቾች ጉዳይ ውሳኔ ሰጥቷል

የኢትዮጵያ መድን ተጫዋቾችን ቅሬታ የተመለከተው የዲስፕሊን ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ውሳኔውን አሳልፏል።

ከሳምንታት በፊት ስምንት የኢትዮጵያ መድን ተጫዋቾች (ያሲን ጀማል ፣ አቤል ማርቆስ ፣ ተስፉ ሚካኤል ፣ አሰግድ ጨዋቄ ፣ ኪዳነ ተስፋዬ ፣ ዘላለም ሊካሳ ፣ ሳሙኤል በለጠ እና በክሪ ማሀመድ) ‘ከክለባችን የተሰናበትንበት መንገድ ትክክል አይደለም ፤ ባለፈው ዓመት ያመጣነውን ውጤት እና የከፈልነውን መስዋዕትነት በማይመጥን መልኩ ከክለቡ የስንብት ደብዳቤ ደርሶናል ፤ ክፍያም አልተፈፀመልንም’ በማለት ለዲስፕሊን ኮሚቴ አቤቱታ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ሁኔታውን ሲመረምር የቆየው የዲስፕሊን ኮሚቴም ውሳኔዎች በማሳለፍ ጉዳዩን ቋጭቶታት። በዚህም ቡድኑ የሰጠው የስንብት ውሳኔ እንዲሻር እና ለተጫዋቾቹ ያልተከፈለው ደመወዝ እንዲከፈል ፌደሬሽኑም በውሳኔው መሰረት እንዲያስፈፅም ኮሚቴው ወስኗል።

በጉዳዩ ዙሪያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸው የሰጡት የኢትዮጵያ መድን ስፖርት ከለብ ፕሬዚዳንት አቶ ተምትም “በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ይሰራል ይባላል። ሆኖም በአንድ በኩል የዲስፕሊን ኮሚቴ ተጫዋቾች ጥፋት እንዳጠፉ በደብዳቤ አሳውቀን እያለ እንዲመለሱ በማድረግ ይከፈላቸው ይላል ፤ አንዱ ይሰራል አንዱ ደግሞ ያፈርሳል። ተቋሙ አሁንም ይግባኝ ይላል። ማንኛውም ተጫዎችም ሆነ የክለቡ አካል በአድማ ሆን ብሎ ለትውልድ የሚተላለፍ ንብረትን የሚያጠፋን አካል ይከፈለው ተብሎ መወሰኑ አግባብነት የሌለው ነገር ነው። ተቋሙ ችግሮቹን ለይቶ በማውጣት ነበር እነዚህን ዓይነት ችግር አለባቸው ብሎ ውሳኔ ቀድሞ ለፌዴሪሽን ያስገባው። እውነቱን ለመናገር በፌዴሬሽኑ ውሳኔ በጣም ነው ያፈርነው። ሆኖም ይግባኝ ጠይቀን ምላሹን ደግሞ በጋራ የምናይ ይሆናል።” ብለዋል።

ለጉዳዩ የተሰጠው ውሳኔ 👇



© ሶከር ኢትዮጵያ