“ይህ ድል ለደጋፊዎቻችን በጣም አስፈላጊ ነበር” ሙጂብ ቃሲም

በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ተጋጣሚው መቐለ 70 እንደርታን 1-0 በማሸነፍ ዋንጫውን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንስቷል። ለድሉ መገኘት ወሳኙን እና ብቸኛውን የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠረው ሙጂብ ቃሲም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል።


የጨዋታው እንቅስቃሴ

ይህን የጨዋታ ቀን በጣም በጉጉት ስንጠብቀው ነበር። ምክንያቱም ለቀጣይ ውድድር ትልቅ መነሳሳት ስለሚሆነን። እንዳያችሁት በደጋፊዎች በኩል የነበረው ድባብ በጣም የምያምር ነበር። በሜዳ ላይም እንቅስቃሴ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ወስደን ተጭነን ነበር የተጫወት ነው። ከአንድ ጎል በላይ አስቆጥረን ማሸነፍ ይገባን የነበረ ቢሆንም ያም ባይሆን በጠባብ ውጤት ማሸነፋችን በጣም አስደስቶኛል።

የማሸነፊያ ብቸኛውን ጎል ማስቆጠር

ዓምና የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ትልቅ ፍላጎት ነበረን። እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርገናል። እንዳጋጣሚ ሆኖ ሳናሳካ ቀርተናል። ደጋፊው የሚፈልገውን የሊጉ ዋንጫ ባለማንሳታችን ደስተኛ ባይሆንም የቀሩትን ዋንጫዎች በማንሳት ደጋፊውን ለመካስ ብዙ ስንጥር ቆይተናል። በመጨረሻም ጥረታችን ተሳክቶ በእኔ ጎል የትናንቱን ዋንጫ ማንሳታችን በግሌ በጣም አስደስቶኛል። በእርግጠኝነት ጎል እንደማስቆጥር ከጨዋታው በፊት አስቤ ነው ወደ ሜዳ የገባሁት። ይህ በመሆኑ ደግሞ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።

የትናንቱ ድል ለቀጣይ ውድድር የሚፈጥረው መነሳሳት

ዓመቱን በዋንጫ ታጅበን መጀመራችን ለእኛ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ለቀጣይ ውድድር ትልቅ ተነሳሽነታችንን የበለጠ ከፍ ያደርገዋል። የተሻለ የማሸነፍ ሥነ-ልቦና ይኖረናል። ቡድናችንም የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ የማንሳት አቅም አለው። ከዚህ በኃላ ሙሉ ትኩረታችን ወደ ሊጉ ውድድር በማድረግ ዓምና ያጣነውን ዋንጫ ለማሳካት ጠንክረን እንሰራለን።

የጎሉ መታሰቢያነት

እንደሚታወቀው ይህ ድል ለደጋፊዎቻችን በጣም አስፈላጊ ነበር። ሁሌም በማንኛውም ነገር ድጋፋቸውን በመስጠት ከእኛ ጋር አብረው እየለፉ ይገኛል። ትናንትም እንዳያችሁት ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን ሲደግፉን፣ ሲያበረታቱን ነበር። የጎሉ መታሰቢያ ለክለባችን የልብ ደጋፊዎች ይሁንልኝ። በመቀጠል የመጀመርያ ሴት ልጅ አባት ነበርኩ በቅርቡ ደግሞ ኹለተኛ የወንድ ልጅ አባት በመሆኔ የጎሉ መታሰቢያ ለልጄ ይሁንልኝ።


© ሶከር ኢትዮጵያ