ፈቱዲን ጀማል በኢትዮጵያ ቡና ስላለው ወቅታዊ አቋም ይናገራል

ኢትዮጵያ ቡናን በተቀላቀለበት ዓመት ከቡድኑ ጋር ተዋህዶ በአምበልነት ጭምር ጥሩ ብቃቱን በማሳየት በደጋፊው ልብ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መግባት ችሏል። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ሁለት ጊዜ የጨዋታው ኮከብ በመባል ብቸኛው ተሸላሚ በመሆንም መልካም የውድድር ጅማሮ አድርጓል።

በሀላባ ከተማ፣ በወላይታ ድቻ፣ በሲዳማ ቡና የተሳካ ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ፈቱዲን ጀማል በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታ እንዲህ ባለ ሁኔታ አሰናድተን አቅርበነዋል።

የአአ ከተማ ዋንጫ ተሳትፎህ የመጀመርያህ ነው። ውድድሩን እንዴት አየኸው ?

በአአ ሲቲ ካፕ ስሳተፍ ይህ የመጀመርያዬ ነው። ለእኔ በግሌም እንደ ቡድንም ጥሩ ጊዜ ያሳለፍኩበት ውድድር ነው። ከዚህ ውጭ በሠላም ዙርያ በደጋፊዎች መካከል የነበረው ኅብረት እና አንድነት ደስ ይል ነበር። እግርኳሱ የሠላም መድረክ እንዲሆን ይሠሩት የነበረው ሥራ፤ ሀገራችን ሠላም እንድትሆን ያደርጉት የነበረው ተግባር በጣም ሊበረታታ የሚገባ ደስ የሚል ነገር ነው።

ኢትዮጵያ ቡናን ዘንድሮ ነው የተቀላቀልከው። የእስካሁን ቆይታህ ምን ይመስላል?

ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ በዝግጅት ወቅት እንዲሁም በአአ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ባለኝ ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ። በጣም እመኘውና እፈልገው ወደነበረ ክለብ መግባቴ ነገሮች እንዳይከብዱኝ እንዲመቸኝ አድርጎኛል። ወደ ሊጉ ውድድርም ስንገባ አሁን ካለኝ በተሻለ ራሴን አዘጋጅቼ ቡናማዎቹን ለማገልገል አስባለው።

እንደተመቸህ የሚያስታውቀው ከቡድኑ ጋር በፍጥነት ተዋህደሀል፤ አምበልም ሆነህ ቡድኑን መርተሀል፣ በደጋፊ ልብም ውስጥ በቶሎ ገብተሀል። ይህ ማሳያ ሊሆን ይችላል ?

አስቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስመጣ ወደ ትልቅ ክለብ፣ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት እና የሚከተለው አጨዋወትም እኔ ከምፈልገው አጨዋወት ጋር የሚሄድ መሆኑን ከግምት አስገብቼ ነው። በሜዳም በልምምድ ወቅት ሥራህን በታታሪነት የምትሠራ ከሆነ የማትወደድበት ምክንያት የለም። ክለቡ እና ደጋፊዎቹ በአንድ ላይ ከወዲሁ በአጨዋወቴ ደስተኛ ሆነው በእኔ እምነት መጣላቸው ትልቅ ብርታት የሚሆን፣ የበለጠ እንድሰራ የሚያነቃቃ እና ክለቡን በኃላፊነት ስሜት እንዳገለግል የሚያነሳሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አሰልጣኝ እና የጨዋታ አቀራረብ መጥቷል። ይህ የጨዋታ ፍልስፍና እናንተ ተጫዋቾች የመቀበል፣ የመላመድ ሁኔታችሁ እንዴት ነው ?

በመጀመርያ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል አዲስ ቡድን ነው። ሁለተኛ አዲሱ አሰልጣኝ ይዞት የመጣው የጨዋታ ፍልስፍና ለመተግበር በዝግጅት ወቅት ሁሉም ተጫዋች ደስተኛ በመሆን ራሱን በአዕምሮ ዝግጁ በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል። በአአ ከተማ ዋንጫም የቡድናችንን እንቅስቃሴ ለማሳየት ሞክረናል። በተወሰነ መልኩ ለደጋፊው እኛም ምን እንደምንፈልግ አሳይተናል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ ያሉ ነገሮች አሉ። የቀሩንን ነገሮች በሲቲ ካፕ ላይ ስላየን በፕሪምየር ሊጉ ላይ ችግሮቻችንን ቀርፈን እንመጣለን ብዬ አስባለው። ሜዳ ላይ ልተገብረው ያሰበው ነገር ሁሉም በትዕግስት እንዲጠብቅ ብቻ ነው የምፈልገው።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአንተ መመረጥ አዲስ አይደለም። ከ20 ዓመት በታች እና በኦሊምፒክ ቡድን ተመርጠህ ተጫውተሀል። ሆኖም በዋናው ብሔራዊ ቡድን ከመጠራት ባለፈ በቂ ግልጋሎት እየሰጠህ አይደለም። በቀጣይ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምን ታስባለህ ?

እንዳልከው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዕድሜዎች ብሔራዊ ቡድን አገልግያለው። በዋናው ብሔራዊ ቡድን ከጥሪ ባለፈ የተጫወትኩበት ጊዜ የለም። ግን አሁን ባለው ነገር የአሰልጣኙ ስራ ነው። ይህ ማለት የመጥራትም ያለመጥራትም ስራ የአሰልጣኙ ነው። ከእኔ የሚጠበቀው ሁልጊዜ ጠንክሬ መስራት ነው። ክለቤ ላይ የማደረግውን አገልግሎት ለሀገሬም ባገለግል በጣም ደስተኛ ነኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ