የ2012 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ዕጣ ወጥቷል

የ2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ዓመታዊ ስብሰባና የ2012 የውድድር ዘመን የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ዛሬ ረፋድ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተካሂዷል።

ዝግጅቱን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የሥራ አስፈፃሚ አባል እና የእግርኳስ ልማትና የሴቶች እግርኳስ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ሶፊያ ኤልማሙን በንግግራቸው አንዳንድ የወንድ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ያላቸው ክለቦች የሴቶች ቡድን ለመያያዝ ሲያቅማሙ መስተዋሉ አግባብነት የሌለው መሆኑን ገልፀው አዲሱ የውድድር ዘመን የሴቶች እግርኳስ ከበጎ ፈቃዳሚ አሰራር ወጥቶ በእቅድ የሚመራበት ለማድረግ ጠንካራ ሥራዎች የምንሰራበት መሆን ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።

በመቀጠልም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የውድድሮች ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ከበደ የ2011 የውድድር ዘመን አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም አቶ ፍቃዱ ጥላሁን ከብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ የ2011 ውድድር ዓመት የዳኝነት አፈፃፀም ሪፖርት ለተሰብሳቢዎች ቀርቧል።

በማስከትልም 2012 የውድድር ደንብ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ በሆኑት ኢንስፔክተር ጌታቸው የማነብርሃን ቀርቧል ፤ በዚህም ዓለምአቀፉ የእግርኳስ የበላይ አካ ፊፋ በቅርቡ በ17 የጨዋታ ህጎች ላይ ባደረገው ማሻሻያ መሠረት የተወሰኑት በአዲሱ የሊጉ ደንብ ላይ እንዲካተት መደረጋቸውን ገልፀዋል። በተያያዘም ሊጎች ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ሥያሜም ለውጥ በማድረግ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ በሚል መጠርያ የሚካሄዱ ይሆናል።

መርሃግብሩ ከሻይ እረፍት መልስ ከተሳታፊዎች በቀሩቡት ሪፖርቶችና በቀጣይ ውድድሩ በምን መልክ መካሄድ አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦች ተሰጥተዋል፤ በሊጉ የሚዲያ ትኩረት ማጣት፣ መውጣት እና መውረድ፣ መርሐግብር አወጣጥና ሌሎች በርካታ ጉዳዩች የተነሱ ሲሆን የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንትና የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ መርሃግብር ከዚህ በታች ባለው መልኩ ቀርቧል።

ፕሪምየር ሊግ

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
መከላከያ ከ አዲስ አበባ ከተማ
ጌዴኦ ዲላ ከ አርባምንጭ ከተማ
አቃቂ ቃሊቲ ከ ሀዋሳ ከተማ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ድሬዳዋ ከተማ
አራፊ – መቐለ 70 እንደርታ

ከፍተኛ ሊግ

ቦሌ ክ/ከ ከ ፋሲል ከነማ
ሻሸመኔ ከተማ ከ ጥሩነሽ ዲባባ
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ከ ልደታ ክ/ከተማ
ኢ/ወ/ስ አካዳሚ ከ ባህር ዳር ከተማ
ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ቂርቆስ ክ/ከተማ

* የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ኅዳር 27 የሚጀምር ሲሆን የከፍተኛ ሊጉ ደግሞ ታኅሳስ 18 ተጀምሮ እስከ ሰኔ 30 የሚደረግ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ