ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ከአሞሌ ጋር ስምምነት ፈፀሙ

የአዲስ አበባ ስታዲየምን በጋራ የሚጠቀሙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ከዳሽን ባንክ (አሞሌ) ጋር የትኬት ሽያጭ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት መፈፀማቸውን በይፋዊ የፌስቡክ ገፆቻቸው ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እንደ መልካም አሰራር ተብሎ ሲነሳ የነበረው የትኬት ሽያጭ ስርዓት መሆኑ ይታወሳል፡፡ በውድድሩ ላይ በዳሽን ባንክ የአሞሌ ዘመናዊ የትኬት ሽያጭ የእጅ በእጅ የትኬት ሽያጩን ሙሉ በሙሉ ከማስቀረቱ ባሻገር የተቀላጠፈ አሰራርን ለመመልከት ችለንም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ይህን በሊጉ ለመቀጠል ሁለቱ የአዲስ አበባ ክለብ የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ከአሞሌ ጋር ስምምነት ፈፅመዋል፡፡

ክለቦቹ በቀጣይ በአዲስ አበባ በሚያደርጓቸው የሊጉ መርሀ ግብሮች ተመልካቾች ወደ ስታዲየም ለመግባት ቀደም ብለው በተመረጡ የዳሽን ባንክ አሞሌ ተቋም በማምራት ትኬት መቁረጥ ይኖርባቸዋል ሲሉ ክለቦቹ ገልፀዋል። በዚህም ከዚህ ቀደም በስታዲየም በር ላይ ሲደረግ የነበረውን የትኬት ሽያጭ ያስቀረ አሰራርም ይሆናል፡፡

ሁለቱ ክለቦች የስታዲየም የመግቢያ ዋጋዎችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን ከፍተኛው 300፤ ዝቅተኛው 20 ብር ሆኗል። ዓመታዊ ክፍያን ከፍለው ለሚመለከቱ ተመልካቾች መታወቂያ እንደሚሰራላቸው እና ቦታቸውም እንደሚከበርላቸውም ጭምር ተጠቁሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ