የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-0 ወልቂጤ ከተማ

በ2ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም ላይ ወልቂጤ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ከባለፈው ጨዋታ ዛሬ ተሻሽለን በመቅረብ ሦስት ነጥብ ይዘን መውጣት ችለናል” ም/አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው

” በመጀመርያ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎችን በሙሉ እንኳን ደስ አላቹየችሁ ማለት እፈልጋለው። ጨዋታውን እንዳያችሁት ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ባለፈው ሳምንት እዚሁ ሜዳችን ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተን ወጥተን ነበር። ከባለፈው ጨዋታ ዛሬ ተሻሽለን በመቅረብ ከጎል ጋር አሸንፈን ሦስት ነጥብ ይዘን መውጣት ችለናል። በቀጣይም በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመጨረስ የሚችል በወጣት የተገነባ ቡድን ይዘን ቀርበናል”።

ከተስፋ ቡድን ስላደጉት ወጣቶች

” እንደሚታወቀው መናፍ ዐወል እና ፉአድ ፈረጃ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ ያለፉትን ዓመታት ይጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው። ዘንድሮ ጊዜአቸውን ጠብቀው በዋናው ቡድን እንዳያችሁት በሁለቱም ተከታታይ ጨዋታዎች የመጀመርያ ተሰላፊ እድል አግኝተው ጥሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛል። በቀጣይ ጠንክረው ከሰሩ ለአዳማ ከተማ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጥቀም የሚችሉ ናቸው”

“ይህ ቡድን እያደገ ሲሄድ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል” ደግአረግ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው

” የሊጉ ሁለተኛ ጨዋታችንን ነው ያደረግነው። ከሜዳችን ውጭ እንደመጫወታችን ልጆቻችን ያሳዩት ጥረት፣ ለማሸነፍ የነበራቸው ቁርጠኝነት በጣም የሚያስደስት ነበር። ሜዳው ላይ እንደነበረን እንቅስቃሴ ውጤቱን መቀየር የምንችልበት አጋጣሚ ፈጥረን መጠቀም አልቻልንም። ነገር ግን አዲስ ቡድን እንደመሆኑ መጠን እግርኳስ ሂደት ነው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ልጆቻችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያየን ነው። ይህ ቡድን እያደገ ሲሄድ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል”።

በተከታታይ ጨዋታ ጎል አለማስቆጠር

” የሜዳው ሦስተኛ ክፍል ላይ ለመድረስ እንደ ቡድን ችግር የለብንም። ልጆቻችን ጥሩ ይንቀሳቀሳሉ፣ የጎል ዕድል የመፍጠር አቅማቸውም ጥሩ ነው። አሁን እኛ ጋር ጎልቶ እየታየ ያለው የተገኙ የጎል እድሎችን ወደ ጎል የመቀየር፣ የመወሰን ችግሮች እያየን ነው። እነዚህ ደግሞ ከልምድ ጋር የሚያያዙ ናቸው። ልጆቻችን በራስ መተማመናቸው ከፍ ብሎ የተሻለ ነገር ለመስራት ይችሉ ዘንድ በየልምምዱ፣ በየጨዋታው እያረምን ለመቅረብ ጥረት እያደረግን ነው። ዛሬም እንዳያችሁት ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። ነገር ግን የተገኙትን የግብ ዕድሎችን መጨረስ ላይ የበለጠ ሰርተን በቀጣይ ጨዋታ ላይ የተሻለ ነገር ይዘን ለመምጣት ጥረት እናደርጋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ