11ኛው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የግማሽ ቀን ውሎ

11ኛው የኢትዮጵያ እግርኳስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬ ከረፋድ አንስቶ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የእግርኳስ ፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላትን ጨምሮ ሁሉም የፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ አባላት በተገኙበት በዚሁ መርሐግብር ላይ የኢፌድሪ ስፓርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩርና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አቶ አሸብር ወልደጊዮርጊስ በተጋባዥነት ተገኝተዋል።

በቅድሚያ የምልዓተ ጉባዔው መሟላቱን በፌደሬሽኑ ዋና ፀኃፊ ኢያሱ መርሐፅድቅ(ዶ/ር) አማኝነት በተደረገው ቆጠራ በጠቅላላ ጉባዔው በድምፅ መሳተፍ ከሚችሉ 146 አባላት ውስጥ 127 አባላት መገኘታቸው ስለተረጋገጠ ስብሰባው እንዲቀጥል ተደርጓል።

ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ስለከወናቸው ተግባሮች አንስተዋል።

በጥንካሬነት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ፡-

– የፌደሬሽኑን ፅሕፈት ቤት መዋቅር ለማሻሻል የሪፎርም ጥናት ተጠንቶ ወደ ትግበራ መገባቱ

-የረጅም ዓመታት ውጥን የነበረውን የፕሪምየር ሊግ ውድድር በተሳታፊ ክለቦች እንዲመራ ማስቻል

-የፌዴሬሽን አሰራርን ለማዘመን በማሰብ በሦስት ቦታ ተበታትንኖ ይሰጥ የነበረውን የፌደሬሽኑን አገልግሎት ለማስቀረት የህንፃ ግዢ መከናወን

– ስፖርታዊ ጨዋነት ለማስፈን በርካታ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን በተጨማሪም ከአጋር አካላት ጋር በሦስት ዙር የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ

– ያለአገልግሎት ለዘመናት የቆየውን የካፍ አካዳሚን ፌዴሬሽኑ ተረክቦ በቅርቡ እድሳ ተደርጓለት ወደ ስራ እንዲገባ እንቅስቃሴ መጀመሩ

– ከዓለም አቀፉ ትጥቅ አቅራቢ አምብሮ ኩባንያ ጋር ለብሔራዊ ቡድኑ ነፃ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት መደረሱ

-ከዋሊያ ቢራ ጋር ለ4 ዓመታት የሚቆይ አዲስ የ56 ሚልየን ብር የስፖንሰር ሺፕ ውል መፈፀሙ

-በሀገሪቱ ከሚገኙ ከተመረጡ 16 የከፍተኛ ትምህርት ተቆማት ጋር በታዳጊዎች ስልጠና ዙርያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ ለትግበራው እንቅስቃሴ መጀመሩ

-የዳኞችን አቅም ለማሳደግ በርካታ ስልጠናዎች መዘጋጀታቸው

በጥንካሬ ከተነሱት ባሻገር በድክመትነት በተለይ በስፓርታዊ ጨዋነት ዙርያ እንዲሁም የፌደሬሽኑ ጠንካራ የሆነ የገቢ ምንጭ አለመኖሩ ቀርበዋል።

በማስከተል የኢፊዴሪ የስፓርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር አጠር ያለ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በመቀጠልም በፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አቅራቢነት የጉባዔው ድምፅ ቆጣሪዎችና ቃለ ጉባዔ አጣሪ ግለሰቦችን በእጩነት ቀርበው በአባላት ድምፅ ከተሰጠባቸው በኃላ እንዲፀድቁ ሆኗል።

በቀጣይነትም ለጉባዔው አስቀድሞ በተላኩት አጀንዳዎች የፀደቁ ሲሆን ከአጀንዳዎች ውስጥ ተካቶ የነበረው የፌደሬሽኑን መተዳደርያ ደንብ ለማሻሻል የቀረበ ውጥን በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በነበረው የፊፋ ኮንግረስ የአባላት መተዳደሪያ ደንብ ወጥ እንዲሆን በቀረበው ምክረ ሀሳብ መሠረት ከአጀንዳ ውጭ እንዲደረግ መደረጉም ተያይዞ ተገልጿል።

በአጀንዳው መሠረት በቅድሚያ የ2011 እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በፌደሬሽኑ ዋና ፀሐፊ የቀረበ ሲሆን በፕሬዚዳንቱ ንግግር የተነሱ ዐቢይ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመዳሰስ ተሞክሯል። በተጨማሪም በዓመቱ ስለገጠሙ ችግሮችና ስለተወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ዘለግ ያለ ማብራሪያ ቀርቧል።

በመቀጠል በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦችና ጥያቄዎች በሪፖርቱ ዙርያ ቀርበዋል ፤ ከእነዚህ መካከል

ከትግራይ ክልል ተወካዮች

-በሁሉም የውድድር እርከን ላይ ይታይ ስለነበረው የውድድር መቆራረጥ ማብራሪያ ቢሰጥ

-በቀረበው ሪፖርት አብዛኞቹ ችግሮችን ወደ ውጪያዊ አካላት ላይ ለማላከክ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ይህም ፌደሬሽኑ እራሱን ገምግሟል ለማለት እጅግ አስቸጋሪ ነው።

– ካፍ በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዙር አጠቃላይ የግምገማ ሰነድ ባላቀረበበት ሁኔታ ውድድሩ ወደ ባህር ዳር መሸጋገሩ ተቀባይነት የሌለው አሰራር ነው። በእኛ እምነት ፌደሬሽኑ ውስጥ ባሉ አካላት በተጠነሰሰ ሴራ ውድድሩ እንዳይካሄድ ስለተደረገበት አካሄድ ፌደሬሽኑ በይፋ ማብራሪያ መስጠት ይገባዋል።

ከደቡብ ክልል ተወካይ

– በሪፖርቱም በፕሬዘዳንቱም ንግግር ላይ አይቮሪኮስትን ማሸነፋችን እግርኳሳችን እያገገመ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ መቅረቡ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አይገፅም።

– በእግርኳስ ውድድር ሜዳዎች ላይ እየታየ የሚገኘው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለማስወገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላትየየድርሻውን ኃላፊነት በጋራ መውሰድ ይገባናል።

– በፕሪምየር ሊግ ተካፋይ የሆኑ የተወሰኑ ክለቦች በፌደሬሽኑ አሰራር እና አካሄድ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት

መንግስቱ ሳሳሞ – ሲዳማ ቡና

– ዐምና በሊጉ አወዳደሪ አካል ይሰጥ የነበሩ ፎርፌዎች በሊጉ የመጨረሻ ውጤት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስለመኖሩ፤ ስለተዘበራረቀው የተጫዋቾች የዝውውር ሂደት በሪፓርቱ አልተገለፀም።

 

የኮንሶ ኒውዮርክ ተወካይ

– አጠቃላይ ሪፖርቱም ሆነ ሀሳቦች እየቀረቡ የሚገኙት ሀሳቦች በወንዶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ብቻ የታጠሩ ናቸው፤ የሌሎች ውድድር እርከኖችን ያካተተ አይደለም። የስፓርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች በአንደኛ ሊግ ከሚታሰበው በላይ እጅግ ሥር የሰደዱ ናቸው።

– የፍትሕ አካላት አሳማኝ ማስረጃ በቀረበበት ሁኔታ እንኳን ተገቢ የሆነ ውሳኔ መስጠት ላይ እጅግ ደካማ አሰራር

ሀረሪ ክልል ተወካይ

– ፌደሬሽኑ በሚያዘጋጀው መድረኮችና መርሐ ግብሮች ላይ ምንም እንኳን የጠቅላላ ጉባዔ አባል ብንሆንም ጥሪዎች በቀጥታ አይደርሱንም።

አፋር ክልል ተወካይ

– የተጠራው ጉባዔ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጉባኤ ቢሆንም የቀረው ሪፖርት አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለውን የእግርኳስ ሁኔታ አይወክልም።

– የኮካ ኮላ ውድድር በተመለከተ ክልሎች ያወጧቸው ወጪዎች በተገቢ ሁኔታ ክፍያዎች አልተወራረዱም።

አማራ ክልል ተወካይ

– የሪፎርም ጥናት ስለመደረጉ በስፋት ተጠቅሷል። ነገር ግን ከጥናት በዘለለ በተግባር ስለተደረጉ ለውጦች በቂ የሆነ ማብራሪያ በሪፖርቱ አልተካተተም።

– የቻን ውድድር ለማካሄድ አቅደን አልተሳካም። በቀጣይ ከዚህ ስህተታችን መማር እንድንችል በነበረው ሂደት ዙርያ ማብራሪያ ቢሰጥበት።

– በኮካ ኮላ ውድድር ዙርያ ፌደሬሽኑ የሚያገኘውን ገቢ በቀመር ለክልሎች መከፋፈል ሲገባው እየተደረገ አይደለም። በተጨማሪም አማራና ኦሮሚያ ክልሎች የውድድሩ አሸናፊ በመሆናችን በአህጉር ደረጃ ለሚደረግ ውድድር ተካፋይ የመሆን እድል ብናገኝም በፌደሬሽኑ ቸልተኝነት መሳተፍ ሳንችል ቀርተናል። ይህም ግልፅ ማብራሪያ ይፈልጋል።

– በዓመቱ የውድድር አፈፃፀም ላይ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ የተሰሩ በጎ እንዲሁም አሉታዊ ችግሮች ካሉ በግልፅነት ማብራሪያ ቢሰጥ።

ገዛኸኝ ወልዴ

– በጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት አቀራረብ ዙርያ ከጥቃቅን ሀሳቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ መቅረብ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ዙርያ የሪፖርቱ ይዘት ማሻሻያ ያስፈልገዋል።

– በሪፖርቱ በጥንካሬነት የቀረቡት ፌዴሬሽኑ እንደ አገልግሎት ሊሰጣቸው የተቋቋሙ ነገሮች እንጂ ይህ ነው የሚባሉ ተግባሮች አይደሉም።

– ከአምብሮ ጋር ስለተገባው ውል ሲገለፅ በነፃ የትጥቅ ማቅረብ ስምምነት ተብሎ የተገለፀው ሀሳብ ከዓለም አቀፍ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ጋር የሚፃረር ነው። ኩባንያው በውሉ ተጠቃሚ ሊሆንበት ስለሚችለው ነገር የተጠቀሰ ጉዳይ የለም፤ ከቀደመው ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ስለነበረው ሁኔታም መብራራት ይገባዋል።

– የ2011 የውድድር ዘመን በግልፅ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ የ2011 የውድድር ዘመን በሰላም ተጠናቋል ተብሎ ሪፖርት ላይ መቅረቡ ተገቢ አይደለም።

አሸናፊ እጅጉ – ከኢኮስኮ

– የፌደሬሽኑ አመራሮች ለአንድ አላማ እስከተሰለፋችሁ ድረስ በጋራ በመነባበብ መስራት ይገባችኃል።

በተነሱት ሀሳቦች ዙርያ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተለይም አብዛኞቹ ከጉባዔው የተነሱ ጉዳዮች በግብዓትነት የሚወሰዱ መሆናቸውና ሪፖርቱ ደካማ ስለመሆኑ አምነው ማብራሪያ ይሻሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ሰጥተዋል።

ስለአይቮሪኮስቱ ጨዋታ ድንገተኛ የስታዲየም ለውጥ

“በቅድሚያ መግባባት የሚገባን የአይቮሪኮስቱን ጨዋታ የስታዲየም ለውጥ ጉዳይ ፖለቲካዊ አጀንዳ ለማስያዝ የሚጥሩ ኃይሎች ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ሌላው ከፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ውስጥ ማንም አባል ውሳኔ የማስቀየር ፍላጎት ያለው ሰው የለም፤ መቐለ የተገኙት ግለሰብ የክለብ ላይሰንሲንግ ባለሙያ ናቸው። እሳቸው ሁኔታውን የተመለከቱት ከክለብ ላይሰንሲንግ እይታ አንፃር ብቻ ነው፤ ነገርግን ሂደቱን በቀጥታ የሚመለከተው የውድድር አስተዳደር አካልን ነው። እኛ መረጃው የደረሰን ከካፍ ኮሙኒኬሽን ክፍል በቀጥታ ነው፤ በተመሳሳይ ባለሙያው አጥሩ አልተጠናቀቀም፤ ከመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያነሳቸው ነጥቦች ነበሩ። ከዚህ አንፃር ቢታይ የተሻለ ነው።”

ስለስፖርታዊ ጨዋነት

“በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ የነበረብንን ህመም በግልፅ የሚገልፅ ሪፖርት አላዘጋጀንም። ነገርግን ዘንድሮ በሁለት ሳምንት ውስጥ መጠነኛ መሻሻሎች አይተናል። እውነታው ግን በብሔር ፖለቲካ የተነሳ ሊግ የተቆረጠበት ሀገር ተብለን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማችን እየተሳ ባለንበት የፊፋው ፕሬዚዳንት ኢንፋንቲኖ በዚች ሀገር ላይ 70ኛው የፊፋ ኮንግረስ ስለመደረጉ ጥርጥሬ ገብቷቸው ልዑክ ልከው እንዲደረግ ማጣራት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ብዙ የቤት ስራ አለብን።
ከዚህ ጉባዔ ስንወጣ ክለቦች የየራሳችንን ድርሻ ተወጥተን ብንሄድ ለሀገራዊ መግባባት አምባሳደር መሆን እንችላለን። በተሰሩ መልካም ጅምሮች ላይ ይበልጥ በማበረታታት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጋግዘን መስራት ይኖርብናል።”

ስለ ኮካ ኮላ ታዳጊዎች ውድድር

“እውነት ለመነጋገር የታዳጊ ተጫዋቾችን ማሳደግ ሳይሆን ዋነኛ ዓላማ ድርጅቱን ማስተዋወቅ ነው። በመንግስት አዲስ በተቀመጠው አሰራር መሠረት ትምህርት ሚኒስቴር ታዳጊ ተጫዋቾች ስልጠና በተመለከተ በዋነኝነት በበላይነት የሚመራው ይሆናል። በተመሳሳይ በአህጉራዊ ውድድሩን በሚመለከት ኮካ ኮላ ቃል የገባውን 124ሺህ ብር በወቅቱ መክፈል ባለመቻሉ ሲዘጋጁ የነበሩ ታዳጊዎችን በማይመለከት ገብተን ከራሳችን ለመክፈል ቼክ ብንፅፍም የውድድሩ መጀመርያ ቀን ስለነበር ሳይሳካ ቀርቷል።

አሰልጣኞች ስልጠና በተመለከተ

“ተጨማሪ ስልጠናዎችን ከመስጠት ይልቅ ያለውንን መፈተሽ ይገባናል። በፊፋና ካፍ ግምገማ መሠረት የምንሰጠው ስልጠና ችግር እንዳለበት ተነግሮናል። ለዚህም በመፍትሔነት በጥናት የደረስንበት ያሉትም አሰልጣኞች በአመዛኙ አቅማቸውን በማሳደግ ረገድ ብዙም ጥረት ሲያደርጉ አይታይም። ለዚህም አጠቃጣይ የስልጠናው ስርዓት መፈተሽ ይኖርብታል። ወደ ካፍ ስልጠና ዘለን ከመሄዳችን በፊት የራሳችንን ብሔራዊ የስልጠና ማንዋል አዘጋጅተን መስራት ይኖርብናል ፤ ይህም እስኪዘጋጅ ድረስ ተጨማሪ ስልጠና አንሰጥም”

በመጨረሻም ስብሰባው ወደ ምሳ እረፍት ከመበተኑ በፊት የቀረበው ሪፖርት ከተሳታፊዎች በተሰበሰበ ድምፅ ሪፖርቱ በ105 ድጋፍ እንዲፀድቅ ተደርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ