ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሰበታ ከተማ

ቅዳሜ የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ማክሰኞ ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሰበታ ከተማ 11:00 ላይ እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

አስቀድሞ በወጣው መርሐ ግብር ቅዳሜ ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በብሔር ብሔሰቦች በዓል ምክንያት የቀን ለውጥ ተደርጎበት ማክሰኞ እንዲደረግ የተወሰነ ሲሆን ለበዓሉ ማክበሪያነት በአዲስ አበባ ስታዲየም የተሰራው የእንጨት ርብራብ ባለመወገዱ ጨዋታውን በሰዓቱ ስለመከናወኑ ጥርጣሬ እንደገባን መዘገባችን ይታወሳል።

አሁን ባገኘነው መረጃ መሠረት ለበዓቱ ማድመቂያነት የተሰራው ርብራብ እየነሳ በመሆኑ ስታዲየሙ ለ11:00 ጨዋታ ዝግጁ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በመጀመርያ ጨዋታው ወደ ባቱ ተጉዞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለ ጎል ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመርያ ሦስት ነጥቡን ለማሳካት ከሌላኛው አዲስ አዳጊ ጋር ይፋለማል። ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እያሳየ እንደሆነ የታየ ሲሆን በዚህ ጨዋታ ለውጦች ካልተፈጠሩ በቀር በከተማው ዋንጫ የተመለከትነውን ዓይነት አቀራረብ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የጎል እድል መፍጠር እና የቅብብል ስህተቶችን ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን ታሳቢ ያደረገ አጨዋወትን እንደሚከተል ሲጠበቅ የሰበታ የመሐል ሜዳ የበላይነትን ለመቆጣጠር ከወልቂጤው ጨዋታ ከተጠቀመው አሰላለፍ በተለየ ተጨማሪ የመሐል አማካይ ሊጠቀምም ይችላል።

ጊዮርጊሶች የጎል እድል በመፍጠር ረገድ ካለፉት ዓመታት ተሻሽለው ቢቀርቡም አሁንም የሳላዲን ሰዒድ ላይ ጥገኛ መሆናቸው እየታየ ይገኛል። ተጫዋቹ በማይሰለፍባቸው ጨዋታዎች ጎል ለማስቆጠር እንደሚቸገርም ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ከወልቂጤ ጋር ባረደገው ጨዋታ ታይቷል። በዚህ ጨዋታ ሳላዲን የማይሰለፍ መሆኑም ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በፈረሰኞቹ በኩል በጉዳት ላይ የሚገኙት ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሳላዲን ሰዒድ፣ ሳላዲን በርጊቾ፣ አሜ መሀመድ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ፓትሪክ ማታሲ እና ለዓለም ብርሀኑ አሁንም በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን መሀሪ መናም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።

አዲስ አዳጊዎቹ ሰበታ ከተማ ኳስን መሠረት አድርገው በፍጥነት ወደፊት በሚደረጉ ቅብብሎች አልያም እንደተጋጣሚያቸው በረጃጅም በሚጣሉ ዲያጎናል ተሻጋሪ ኳሶች መጠቀምን ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ። ነገርግን በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በወልዋሎ ሲሸነፉ ወልዋሎዎች የሰበታን የመሀል ሜዳ ኳስ ቅብብል ለማክሸፍ አቅደው መግባታቸውን ተከትሎ ሁለተኛ አማራጫቸውን በረጃጅም ኳስ ለመጠቀም ቢጥሩም በጨዋታው የሥራ ፈቃዱ በወቅቱ ባለማለቁ የተነሳ መሰለፍ ያልቻለው ባኑ ዱዋርያ አለመኖሩን ተከትሎ በምትኩ የተሰለፈው ፍፁም ገ/ማርያም የአየር ላይ ኳሶችን ከግዙፉቹ የወልዋሎ የመሀል ተከላካዮች ጋር ተሻምቶ በማሸነፉ ረገድ ደካማ ስኬት በማስመዝገቡ ቡድን በማጥቃቱ ረገድ ፍፁም ተዳክሞ ተስተውሏል። ምናልባት በዛሬው ዕለት ዲያዋራ እንደሚሰለፍ የሚጠበቅ መሆኑ ችግሩን ሊቀርፍ ይችላል ተብሎ ቢገመትም ከተደራጀው የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል ከባድ ፍልሚያ ይጠብቀዋል።

ሰበታ ከተማ ባለፈው ሳምንት ቀይ ካርድ የተመለከተው አዲስ ተስፋዬን በቅጣት እንዲሁም አንተነህ ተስፋዬን በጉዳት አይጠቀምም። የውጪ ዜጋ ተጫዋቾቹን ደግሞ የሥራ ፈቃድ ጉዳያቸው በመጠናቀቁ የሚያሰልፍ ይሆናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ከስምንት ዓመታት በኋላ ይገናኛሉ። በአጠቃላይ በሊጉ ስድስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። በሁለቱ አቻ ሲለያዩ በአንዱ ሰበታ አሸንፏል።

– በስድስቱ ጨዋታዎች ዘጠኝ ጎሎች ሲቆጠሩ ስድስቱን ጊዮርጊስ ሦስቱን ሰበታ አስቆጥረዋል።

– ለመጨረሻ ጊዜ የገናኙት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፍፃሜ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-4-2/4-1-3-2)

ባህሩ ነጋሽ

አብዱልከሪም መሐመድ – ኤደዊን ፍሪምፖንግ – ምንተስኖት አዳነ – ሄኖክ አዱኛ

አቡበከር ሳኒ – ሙሉዓለም መስፍን – ያብስራ ተስፋዬ – አቤል ያለው

አቱሳይ ኤንዶ – ዛቦ ቴጉይ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ጌቱ ኃይለማርያም – ሳቪዮ ካቩጎ – ደሳለኝ ደባሽ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ

መስዑድ መሐመድ – ታደለ መንገሻ – ዳዊት እስጢፋኖስ

በኃይሉ አሰፋ – ባኑ ዲያዋራ – አስቻለው ግርማ


© ሶከር ኢትዮጵያ