የሰበታ ከተማ እና ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት [ዝርዝር መረጃ]

ሰበታ ከተማ ከሜታ አቦ ቢራ ጋር ለአራት ተከታታይ ዓመታት የሚቆይ የገንዘብ እና የስፖርት ቁሳቁስ የስፖንሰር ስምምነት ትናንት ማምሻውን አካሄደ።

በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል የተካሄደው የስፖንሰርሺፕ ስምምነት መርሐ ግብር ከተያዘለት በአንድ ሰዓት ዘግይቶ ጀምሯል። በአባ ገዳ ፀሎት እና ምረቃ በጀመረው በዚህ ሦነ ስርዓት ላይ የክለቡ የበላይ ጠባቂ እና የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ በመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

” በቅድሚያ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተቀላቀልን ማግስት ከአንጋፋው ሜታ ቢራ ጋር በምናደርገው ታላቅ ስምምነት ላይ በመገኘቴ ደስታ ይሰማኛል። ሰበታ ክለብ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በመንግስት በጀት እየተደገፈ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ ደርሷል። ለዚህም የቀድሞ አመራሮችን አመሰግናለሁ፤ ሜታ በከተማችን በማኅበራዊ ተሳትፎዎች ዘርፍ እያደረገ የሚደርገው እገዛ ቀላል አይደለም። አሁን ደግሞ ክለባችንን እንዲደግፍ በጠየቅነው ጥያቄ መሠረት ሰበታ ከተማን ለመደገፍ የአራት ዓመት ስምምነት በመፈፀማቹ እናመሰግናለን። ስምምነቱ ለአራት ዓመት የተገደበ ሳይሆን ጠንክረን በመስራት ጉዛችንን ረዥም እንደምናደርገው ላረጋግጥላቹ እፈልጋለው።” ብለዋል።

የሜታ ቢራ የማርኬት ክፍል ኃላፊ ኔታልያ ሴላኒ በበኩላቸው ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሠላም ሽልማት በማግኘታቸው እጅግ ደስ ብሎናል። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ይህ ስምምነት በዚህ ደስታ ማግስት መሆኑ ደግሞ የበለጠ አስደስቶኛል። ኢትዮጵያውያን ለእግርኳስ ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን እግርኳስን ሲጫወቱ ጥሩ ክህሎት ያላቸው መሆናቸውን እናውቃለን። ሜታ ቢራ ከ50 ዓመት በላይ ያስቆጠረው ፋብሪካው ምስረታውን ያደረገው በሰበታ ከተማ ላይ መሆኑ ሜታ እና ሰበታ ከተማ እግርኳስ ክለብ ያላቸውን ትስስር የረዥም ዓመት ነው። ክለቡ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ መንገዶች ፋብሪካችን ሲደግፍ ቆይቷል። ሰበታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመግባቱ በጣም ደስ ብሎናል፤ ኩራትም ተሰምቶናል። አሁን ደግሞ መደሰት ብቻ ሳይሆን ከጎኑ ሆነን አንድ ላይ ልንሰራ፣ ክለባችንን አብረን ልደግፍ እዚህ ተገኝተናል። ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን። መደሰታችን እና አጋር መሆናችንን በተግባር ለመግለፅ ይኸው የስፖንሰር ስምምነት ፈፅመናል” ብለዋል።

በመቀጠል በክለቡ ፕሬዝደንት አቶ ኦብሳ ለገሰ እና የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ማርኬት ክፍል ኃላሚ ኔታልያ ሴልኒ በመሆን የስምምነት ፊርማ ከተፈራረሙ በኋላ የተዘጋጀውን የደስታ ኬክ ሁሉም ኃላፊዎች በተገኙበት ቆርሰዋል። በመጨረሻም ስምምነቱን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ሰበታን በመወከል ፕሬዝደንቶ ኡብሳ እና ከሜታቢራ ፋብሪካ ተወካይ በጋራ በመሆን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ኡብሳ ” በስምምነቱ መሠረት ሰበታ ከተማ በማልያው ላይ ምርቱን ያስተዋውቃል። በዚህም በአራት ዓመታት ውስጥ ተከፋፍሎ የሚከፈል ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እና አራት ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ የስፖርት ቁሳቁሶችን በማስመጣት ክለቡ ለገበያ አቅርቦ ተጠቃሚ (አትራፊ) እንዲሆን በድምሩ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ የስፖንሰር ስምምነት ነው የተፈፀመው። የመጀመርያው ዙር የዚህ ዓመት የገንዘብ ክፍያ 3.5 ሚሊዮን ብር ነው። ይህም ገንዘብ ወጪ በመሆን በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ የመጫወቻ ሜዳውን ለጨዋታ ምቹ ለማድረግ የእድሳት ስራ እየተሰራበት ነው። ሜዳውን የመስራት ሂደት አስራ አምስት ቀናት አስቆጥሯል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ስራው በጥሩ መንገድ እየሄደ ይገኛል። በተያዘለት ጊዜ መሰረት የስታዲየሙ ሜዳ ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን። ከሜታ ጋር የሚኖረን ስምምነት በዚህ የሚቆም አይደለም፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

” ሌላው በቅርቡ የምንረከባቸው የስፖርት ቁሳቁሶች አሉ ለምሳሌ ለ3 ሺህ ደጋፊዎቻችን የሚሆን የሰበታ ማልያ አሰምመጥተን ለደጋፊዎቻችን በመሸጥ ክለቡን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝ ለማድረግ እንሰራለን ። በቀጣይ ክለቡን ህዝባዊ ለማድረግ እና የገንዘብ አቅሙን ለማሳደግ ያቀድናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እርሱም አጠናክረን እንሰራለን። ”

የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ተወካይ መንግስት ከቢራ ምርቶች የማስታወቂያ ገደብ ጋር ተያይዞ ባወጣው አዋጅ ዙርያ ሲናገሩ ” ያለውን ስጋት እንደ ድርጅት አይተነዋል። የወጣው አዲሱ አዋጅ ቢኖርም እኛ ክለቡን ለመደገፍ ትክክለኛ መንገድ መሆኑን እናምናለን። የሰበታ ከተማ እና በፋብሪካው መካከል ያለው ስሜታዊ ግኑኝነት ዙርያ ትልቅ አንድነት የሚፈጥር በመሆኑ የአዋጁ መውጣት ተፅዕኖ አያደርግም ብለን እናስባለን። በቀጣይ ክለቡ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ፋብሪካችን መደገፉን ይቀጠላል ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ