የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዙርያ የተለያዩ መረጃዎች ስታቀርብላችሁ የቆየችው ሶከር ኢትዮጵያ እንደተለመደው የሁለተኛ ሳምንትንም በቁጥራዊ መረጃዎች እና እውናዎች ታገባድዳለች።

ጎሎች

– በዚህ ሳምንት ባልተለመደ ሁኔታ በርከት ያሉ ጎሎች ተቆጥረዋል። ለወትሮው ሀሜታ በሚበዛባቸው የመጨረሻ የውድድር ወቅቶች በዛ ያሉ ጎሎች የሚቆጠሩበት ሊጉ በዚህ ሳምንት 22 ጎሎች ተቆጥሮበት ለተመልካች ተዝናኖትን ፈጥሯል።

– በዚህ ሳምንት የተቆጠሩ ጎሎች ብዛት ባለፈው (አንደኛ ሳምንት) ከተቆጠሩት በ9 ጎሎች ብልጫ አለው።

– ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባጅፋር ያደረጉት የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐ ግብር ብቻ ጎል ሳይቆጠርበት ተጠናቋል። በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ ቢያንስ አንድ ጎል ተቆጥሯል።

– ባህር ዳር ከመቐለ፣ ፋሲል ከ ድሬዳዋ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከ ሽረ 5 ጎሎች ተቆጥሮባቸው የሳምንቱን የጎል ሚዛን ከፍ አድርገውታል።

– ከተቆጠሩት 22 ጎሎች 20 ጎሎች በክፍት ጨዋታ የተቆጠሩ ሲሆን አንድ በቅጣት ምት፣ አንድ በፍፁም ቅጣት ምት ተቆጥረዋል። 18 ጎሎች በእግር ተመተው ሲቆጠሩ ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባር ገጭተው ከመረብ ያረፉ ናቸው።

– ከ22 ጎሎች መካከል 19 ጎሎች የተቆጠሩት ከተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ተመተው ሲሆን ሦስት ጎሎች ደግሞ ከሳጥን ውጪ የተቆጠሩ ናቸው።

– ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ከተቆጠሩት ጎሎች መካከል ደግሞ አዲስ ግደይ፣ ሙጂብ ቃሲም እና ፍፁም ዓለሙ በራሳቸው የግል ብቃት ኳሱን ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ይዘው በመግባት ያስቆጠሯቸው ናቸው።

– በዚህ ሳምንት የተቆጠሩት 22 ጎሎች በ18 የተለያዩ ተጫዋቾች የተቆጠሩ ናቸው። ሙጂብ ቃሲም በሦስት ጎል የሳምንቱ ከፍተኛ አስቆጣሪ ሲሆን ሽመክት ጉግሳ እና አዲስ ግደይ ሁለት በማስቆጠር ተከታይ ናቸው።

– ተጫዋቾቾቹ በየጨዋታው በተሰለፉበት የመጫወቻ ሥፍራ ስንመለከተው ከ22 ጎሎች መካከል ስምንት የመስመር አጥቂዎች 10 ጎሎች በማስቆጠር ቀዳሚዎች ናቸው። ሰባቱ የተቆጠሩት በአምስት ፊት አጥቂዎች ሲሆን 3 ጎሎች በሦስት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች፣ ሁለት ጎሎች በሁለት አማካዮች ተቆጥረዋል።

– በሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች ጅማ አባ ጅፋር፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ እስካሁን ጎል አላስቆጠሩም።

መጀመርያዎቹ

– በአንደኛው ሳምንት በርከት ያሉ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሁነቶች ተከስተዋል። በዚህ ሳምንት የመጀመርያው ሐት-ትሪክ በፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ሲመዘገብ፤ የመጀመርያው የቅጣት ምት ጎል በሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ አማካኝነት ተመዝግቧል። በአንድ ጨዋታ ሁለት ኳሶችን በማመቻቸት ደግሞ የፋሲል ከነማው ሰዒድ ሀሰን እና የባህር ዳር ከተማው ወሰኑ ዓሊ ሆነዋል።

ካርዶች

– በስምንቱም ጨዋታዎች የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተመዘዋል።

– በማስጠንቀቂያ ካርዶች ብዛት የዚህ ሳምንት ከመጀመርያው ሳምንት እጅግ የላቀ ሆኗል። በስምንቱ ጨዋታዎች በአጠቃላይ ለ33 ተጫዋቾች እና አንድ አሰልጣኝ (ጳውሎስ ጌታቸው) ካርድ ሲመዘዝ ከባለፈው ሳምንትም በ21 ብልጫ አለው።

– በርካታ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመዘዘበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር ሲሆን ፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ለስድስት ተጫዋቾች እና አሰልካኝ ጳውሎስ ጌታቸው ቢጫ ካርድ መዘዋል። የባህርዳር እና መቐለ እንዲሁም የሆሳዕና እና ሀዋሳ ጨዋታ በአምስት ካርዶች ተከታዩን ደረጃ ይዟል።

– በዚህ ሳምንት ምንም ቀይ ካርድ አልተመዘገበም።


© ሶከር ኢትዮጵያ