ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

አስገዳጅ የሜዳ ለወጥ ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ጠንካራው ፋሲል ከነማን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን በሚከተለው መልኩ ተዳሷል።

ሜዳ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ቢያሳዩም በውጤት ለማጀብ የተቸገሩት ወልቂጤዎች በ3ኛ ሳምንት አስደናቂ ሳምንት ካሳለፉት ፋሲል ከነማ ጋር የሚገናኙ ይሆናል። በመርሐ ግብር አወጣጥ እድለኛ የማይመስሉት ወልቂጤዎች በመጀመሪያ ሦስት ሳምንት በሊጉ ከሚገኙ ጠንካራ ቡድኖች ጋር በተከታታይ ለመጫወት ተገደዋል። በአንፃሩ ፋሲል ከተማዎች በመጀመሪያ ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ነጥብ ቢጋሩም በ2ኛ ሳምንት በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ድሬዳዋ ላይ የግብ ናዳን ማዝነብ ችለዋል።

ኳስን ለመቆጣጠር ቅድሚያ የሚሰጡት ወልቂጤ ከተማዎች አሁንም ቢሆን ኳስን ከማንሸራሸር በዘለለ የተጠና የግብ እድሎችን መፍጠሪያ ስልቶች ላይ ችግሮች እንዳሉበት በግልፅ የሚታይ ነው። በተመሳሳይም የቡድኑ የፊት አጥቂ ቶጎዋዊው ጃኮ አራፋት የቡድን ተጫዋች ካለመሆኑ የተነሳ በተሻለ አቋቋም ላይ የሚገኙ የቡድን አጋሮቹ ተጠቃሚ ሊሆንባቸው የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎች ሲባክኑ ይስተዋላል። በተጨማሪም አዳነ ግርማን በተጫዋችነት በተጠቀመበት የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ቡድኑ በማጥቃቱም በመከላከሉም ረገድ ሚዛናዊ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል። ሆኖም በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ቡድኑ አዳነ ግርማን አለመጠቀሙ እንደክፍተት የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ወልቂጤ ከአዳነ ግርማ በተጨማሪ ወሳኝ ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱን አለማሰለፉ መጥፎ ዜና ሲሆን ይበልጣል ሽባባው እና ጫላ ተሺታም ሌሎች አገልግሎት የማይሰጡ ተጫዋቾች ናቸው።

ማጥቃትን ተቀዳሚ ምርጫው ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች አብዛኛው የማጥቃት እንቅስቃሴን በተለይ ከጥልቅ ከሚነሳው ሱራፌል ዳኛቸው የሚጀምር ሲሆን ከመስመር እየተነሳ ወደ መሀል አጥብቦ በተቃራኒ ቡድን መስመሮች መካከል በተደጋጋሚ በመገኘት አደጋ ለመፍጠር የሚታትረው ሽመክት ጉግሳ ሌላኛ የጨዋታውን ሂደት መወሰን የሚችል ተጫዋች ናቸው። ከተከላካዮች ፊት የተከከፈቱ ቦታዎች ሲገኙ በቀጥታ አክርሮ ከፈግቦችን ከማስቆጠር በተጨማሪ ሌላኛው የቡድኑ ሰሞነኛ የጥቃት መሰንዘሪያ አማራጭ የሆነው ወደ መስመር ኳሶችን በፍጥነት በማውጣት ከመስመር በሚሻገሩና ከበረኛው ፊት ያለውን ክፍት ቦታ ላይ በሚጣሉ ኳሶች ተደጋጋሚ ግቦችን ሲያስቆጥሩ ይስተዋላል።

በተጫዋቾች ጉዳት ረገድ እንየው ካሳሁን፣ ሰለሞን ሀብቴ፣ ኤፍሬም ክፍሌ (አገግሟል)፣ ጀማል ጣሰው፣ አብዱራህማን ሙባረክ እና መልካሙ ታውፈር (አገግሟል) በጉዳት ላይ ቢገኙም ወሳኝ ተጫዋቾቹ ከጉዳት ነፃ ሆነው ለጨዋታ ይቀርባሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዳነ በላይነህ – ዐወል መሐመድ – ዳግም ንጉሴ – አቤኔዘር ኦቴ

አልሳሪ አልመሐዲ – በረከት ጥጋቡ – ዓባይነህ ፌኖ

ሄኖክ አወቀ – አህመድ ሁሴን – ጃኮ አራፋት

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሳማኬ ሚኬል

ሰዒድ ሀሰን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ጋብሬል አህመድ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ሙጂብ ቃሲም – ኢዙ አዙካ


© ሶከር ኢትዮጵያ